'ጥቁር ጠባሳ'

119
    ትንሳኤ ገመቹ (ኢዜአ)፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ያጋጠማትን  የዜጎች ሞት፣ መፈናቀል ንብረት መውደም እንዲሁም በሰላም ወጥቶ መግባት ያለመቻል ስጋት አስነዋሪ ስለመሆኑ በተደገጋሚ ሲወሳ ቆይቷል።  በዚህ ጉዳይ ላይ በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጣቸውን አሰምተዋል፤ ጭንቀታቸውን ሌሎች እንዲጋሯቸው ድምጻቸውን ከፍ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራርያ ሲሰጡ አገሪቷ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጋጠማትን ፈተና ’’የኢትዮጵያ የወደፊት ጥቁር ጠባሳ’’ በማለት ነው የገለጹት። በእነዚህ ጊዜያት የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የገባበት፣ የመንጋ ፍርድ የታየበት፣ የዘርና ብሄር ተኮር ጥቃቶች የተከሰቱበት፣ ሞትና መፈናቀል እዚህም እዚያም የታየበት ነው። በእነዚያ ወቅት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህልውና አደጋ የተጋረጠበት ነው። ከውጭ ወራሪ ጠላት ሲመጣ መንጋው እንደተነካ ንብ 'ሆ' ብሎ ጠላትን ድባቅ የመምታት ታሪክ ፣ ለዘመናት በመተሳሰብ በመከባበርና በአንድነት የኖረ ጠንካራ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴት ያለው አገርና ህዝብ ይህ ዓይነቱ ክስተት ማጋጠሙ ያልተለመደ ነው። ያለምንም የዘር ልዩነት አጠገቡ ያለውን ወንድምና እህት አድርጎ የሚያይ፣ በክፉ ቀን የሚደርስ፣ ሲመሽበት ተንከባክቦ የሚያሳድር፣ ያለውን የሚያቋደስ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ባህሪ ሊያሳይ ቻለ? የሚለው ያነጋግራል። በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ህዝቡ ተስፋ በሰነቀበትና የተሻለ ነገር በሚጠብቅበት ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ግድያው፣ መፈናቀሉ እንዲሁም ዘረፋው ተባብሶ መታየቱ አዲስ ክስተት ነው። ይህ አይነቱ ድርጊት ለእኛ ኢትዮጵያውያን ፈጽሞ መገለጫ ሊሆን አይችልም። አያት ቅድመ አያቶቻችን ያወረሱን መቻቻል፣ መተባበርና መተሳሰብ ብሎም ጀግንነት መሆኑን የምንዘነጋው አይደለም። ልዩነቶቻችን ውበታችን መሆኑን ስንሰብክ የኖርን፣ ከሃይማኖት እስከ ዘር ብዝሃነታችንን አምነንና ፈቅደን ተቀብለን በጋራ የመኖር የጥንት ታሪክ ባለቤቶች መሆናችንን ዓለም ያወቀልን ነን። እኛ ስንፋቀር የማይቻል የሚመስለውን ሰርተን ያሳየን፤ በሰው አክባሪነታችንና በእንግዳ ተቀባይነታችን አለም ያደነቀንም ነን። የራሳችንን አጉድለን ለሌሎች መሙላት የሚያስደስተን ኢትዮጵያዊነት መልካምነት፣ ኢትዮጵያዊነት ቅንነት፣ ኢትዮጵያዊነት አብሮነት መሆኑን በተግባር ስንገልጽ የኖርን ህዝቦች ነን። ታድያ ይህ መተሳሰብ ይህ መከባበርና አብሮነት እዚህ ግባ በማይባሉ ባልተጨበጡና በማያሳምኑ ምክንያቶች ሰላማችንና ፍቅራችንን ለምን ያሳጡናል? ለሌሎች መልካም አርዓያ የሆንባቸው እሴቶቻችን አሁን ላይ ለምን መዘባበቻ እንሆንባቸዋለን? ወዴትስ ሄዱ? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት መመርመር ያሻናል። ለዘመናት የኢትዮጵያ መገለጫ የነበረውን ድህነትና ኋላ ቀርነት ታሪክ ለማድረግ በምን ፍጨረጨርበት፣ ህዝቡ ተስፋና መነቃቃት ባሳየበት  ወቅት የዚህ ዓይነቱ ክስተት አላስፈላጊ ከመሆን ባለፈ አለም ለደረሰበት የአስተሳሰብ ልቀት የማይመጥን ነው። ከሁከትና ብጥብጥ ከግጭትና ጦርነት ትርፍ ያገኘ አገር የለም። ሊኖርም አይችልም። ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ያጣል፣ ለዓመታት የገነባውን ንብረት ያወድማል። ቁሳዊ ሀብቱንና መንፈሳዊ እሴቱን ይቀማል። ብዙ አገሮችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። እንደቀልድ በተጀመሩ የአደባባይ አመፆች የንጹሃን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ፣ ሃብትና ንብረት ሲወድም በየቀኑ በመገናኛ ብዙሃን የምናየውና የምንሰማው የዕለት ተዕለት ክስተት ነው። የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅና አፍጋኒስታንን ስለሆኑት ከመገናኛ ብዙሃን ያልሰማና ያላየ አይገኝም። የአገሮቹ ዜጎች በአሁን ወቅት የሚናፍቁት ዴሞክራሲን ሳይሆን ሰላምን ነው። በእነዚህ አገሮች ምክንያታቸው ቢለያይም እንደቀልድ በተጀመሩ ሁከትና ብጥብጦች የህዝቦች በሰላም ወጥቶ የመግባት ሰብዓዊ መብት ተገፏል፤ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል። “ጆሮ ያለው ይስማ፤ ልብ ያለው ልብ ይበል” እንዲሉ አበው እነዚህ አገሮች ቀደም ሲል የራሳቸው ባህል፣ ቅርስ፣ ታሪክና ማንነት ነበራቸው። አገሮቹ ይመኩባቸው የነበሩ ቁሳዊ ሀብቶችና መንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ እሴቶች አሏቸው። ነገርግን ከጊዜ በኋላ ባጋጠማቸው የሰላም እጦት ግን ቅርሶቻቸው ወድመዋል፣ ታሪካቸው ጠፍቷል፣ መልከዓ ምድሩ ሕጻናት ከሚቦርቁበት የሰላም ቀጣናነት ወደ ጦርነት አውድማነት ተቀይሯል። ከላይ የጠቀስናቸውን አገሮች እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከሰላም እጦት ጋር ተያይዞ በየቀኑ በርካታ ጉዶች ይሰማሉ። የሰላም እጦት ባጋጠማቸው አገሮች በየቀኑ ሞት፣ ረሃብ፣ ስደትና እንግልት መስማት የተለመደ እየሆነም መጥቷል። አሁን በአገራችን እየተስተዋለ ያለው መተነኳኮስ ወደ እዚያ ስላለመድረሱ ምን ዋስትና ይኖራል? ቀድሞ መስመር ማስያዝ የግድ የሚል ነው። ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰላም እጦትም በርካታ ዜጎች ህይወታቸውን እንዲያጡ አድረጓል። ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ይህ ክስተት ታዲያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱም በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ እየፈጠረ ያለው። መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ለምን አስቀድሞ መከላከል አልቻለም? ወንጀሎች ከተፈጸሙ በኋላስ የወንጀሉን ፈጻሚዎችና ተባባሪዎች በአፋጣኝ ለህግ አያቀርብም? የሚሉ ጥያቄዎችም በስፋት ሲነሱ ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) በቅርቡ በምክር ቤቱ በነበራቸው ቆይታ ከሰላምና ጸጥታ፣ ከህግ የበላይነት መረጋገጥን ጨምሮ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች  ላይ ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምክር ቤቱ አባል አቶ ግዛው ዮሃንስ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉን፣ ንብረት መውደሙንና ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ያነሳሉ። መንግስት እንዲህ አይነት ችግር በአገሪቷ እንዲፈጠር ያደረጉ ወንጀል ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ላይ የወሰደው አስተማሪ እርምጃ ካለ ለምክር ቤቱ እንዲብራራና በቀጣይም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት ያንጸባርቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቷ የተከሰቱ የግድያና የማፈናቀል ተግባራት አስነዋሪና ጭካኔ የተሞላበት ኢትዮጵያም እንደ አገር የተፈተነችበት መሆኑን ነው ለምክር ቤቱ ያብራሩት። በአገሪቷ እዚህም እዚያም የተከሰቱት ችግሮች የፖለቲካ ዓላማ ያላቸውና የመንግስትን አቅጣጫ ለማስቀየር ታቅደውና ተጠንተው የተደረጉ ነበሩ። በየቦታው በተፈፀሙ አሰቃቂና አስነዋሪ ወንጀሎች ተጎጂ ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል ያለመኖሩን ነው ያወሱት። ይህም የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈፀም የተተገበሩ ድርጊቶችን መሆናቸውን ነው ዶክተር አብይ ያመለከቱት። እየተስተዋለ ያለው የስርዓት አልበኝነትና የህግ የበላይነት የማስከበር ፈተና ህዝብና መንግስት ተጋግዘው መፍትሄ ካላበጁለት የአገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው። ለዚህ ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸውን አገሮች እንደ አብነት መውሰዱ ተገቢ ነው። በኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዜጎች በራሳቸው ዜጎች ላይ የፈፀሟቸው ግድያና መፈናቀል የአገሪቷ የወደፊት ጥቁር ጠባሳ  ሆኖ በታሪክ የሚመዘገብ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። ይሁንና የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ሲፈጸም መንግስት አፋጣኝ እርምጃ አለመውሰዱ ብሎም ጉዳዩ በቀላሉ መታለፉ ችግሩ እንዲባባስና ስር እንዲሰድ የራሱ ድርሻ እንደነበረው ዜጎች ይገልጻሉ። የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ወላጆች ጭምር በአገሪቷ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መንግስትም ህግን የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ በየጊዜው ሲያሳስቡም ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቀደም ሲል በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የታየው ስርዓተ አልበኝነት እንዳይደገምና ያለፈው ጥቁር ጠባሳን ለመፋቅ የህዝብና መንግስት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ። በየቦታው የተከሰቱ ግጭቶችን ማስቆም፣ እምቅ የግጭት አቅም ያለባቸውን ቦታዎች በመለየት ግጭቶች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ማምከንና መከላከል እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ማስፈን መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት በሰላምና ጸጥታ ላይ ያከናወናቸውነ ተግባራት ነበሩ። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሃይል የመጠቀም ስልጣን አለው። ይሁንና ከማስተማር ጀምሮ ችግሮች ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እንዲፈቱ እያደረገ ነው። "በጉልበት ህግ ማስከበር ቢቻል ኖሮ ደርግ አይወድቅም ነበር" በማለትም በጉልበት የሚመጣ መፍትሄ አለመኖሩንም ነው ለምክር ቤቱ ያስረዱት። ይሁንና በወንጀል ድርጊቱ እጃቸው አለባቸው የተባሉ ግለሰቦች ህግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተዋል። ባለፉት ወራት በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈፀሙ ወንጀሎች ከ1 ሺ700 በላይ ሰዎች ለህግ መቅረባቸውንና መንግስት ወንጀለኞች ወደ ህግ ማቅረቡን በጥናት እየተመሰረተ የሚቀጥልበት ተግባር መሆኑንም ነው ለምክር ቤቱ ያብራሩት። ከእነዚህም ውስጥ ከአንድ ሺ በላይ በደቡብ ክልል እና ሀዋሳ፣ ከ300 በላይ በቡራዩ፣ ከ80 በላይ በአዲስ አበባ እንዲሁም በሌሎች አካባቢ በወንጀል ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል። በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ወደ ህግ ለማቅረብ ዝርዝር መረጃ የሚያስፈልግ በመሆኑ የማጥራት ስራ እየተሰራ ነው። በቅርቡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ዝርዝር መረጃ  ይፋ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የጠቆሙት። ያለፉትን ዓመታት ጥለውት የሄዱትን ጥቁር ጠባሳ ለመሻር ሰላም  ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ  የሰላሙ ጠባቂ ባለቤት እኔ ነኝ በማለት ከመንግስት ጋር ተባብሮ ኃላፊነት ወስዶ መስራት ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ አለን ብለን በሙሉ ልብ የምንኩራራበት ሰላማችንን መጠበቅ ካልቻልን ከላይ የጠቀስናቸው አገሮች ዕጣ ፈንታ እንደማይደርሰን በምን እርግጠኛ መሆን እንችላለን?      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም