የየም ልዩ ወረዳ ዓመታዊው የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ በቦር ተራራ ተካሄደ

192
ጅማ ጥቅምት 18/2011 በየአመቱ ጥቅምት 17 ቀን በየም ልዩ ወረዳ የሚካሄደው የባህል መድኃኒት ለቀማ ትናንት  በቦር ተራራ ተካሄደ፡፡ የተለቀሙት መድኃኒቶች ለሰው እና ለእንስሳት የሚሆኑት ተለይተው እስከ መጭው አንድ አመት ድረስ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተገልጿል፡፡ በየም ብሔረሰብ አጠራር "ሳሞ ኤታ" ተብሎ  የሚጠራውን  ባህላዊ መድኃኒ  ከእጽዋት ቅጠላ ቅጠል፣ ስራ ስሮችና ቅርፊቶች የሚገኝ ሲሆን ሁሉም የብሄረሰቡ አባላት ባሳተፈ መልኩ ይህንኑ ባህላዊ መድሃኒቱን የመልቀም ስራ ትናንት ተካሄዷል፡፡ የባህላዊ መድኃኒት ለቀማው በየም ልዩ ወረዳ የተለያዩ አከባቢዎች የሚካሔድ ቢሆንም ከወረዳው ቀበሌዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ዓመታዊውን የለቀማ ስነ ሥርዓት በቦር ተራራ ላይ አካሂደዋል፡፡ በባህል መድኃኒት ለቀማ  የተሳተፉት አቶ አዳነ ኃይለማሪያም  እንደገለጹት "የቦር ተራራ የመጀመሪያውን የማለዳ ጸሐይ ቀድሞ የሚያገኝ በመሆኑ በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ዕፅዋት በሸታን የመከላከልና የመፈዋስ አቅም አላቸው ብለን ስለምናምን  የዘንድሮውን የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ በተራራው አድርገናል" ብለዋል፡፡ ለባህላዊ መድኃኒትነት የሚለቀሙት እፅዋት ህመምን ከመፈውስ  በተጨማሪ  በምግብ ውስጥ በተለይም በገንፎ ተነስንሰው ሲበሉ የምግብ ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ተሳታፊ ወጣት አለሚቱ ጀንበሬ በበኩሏ ከዕጸዋቱ የሚለቀሙት መድኃኒቶች  ለተለያዩ በሽታዎች  ፈውስ እንደሚሆኑ ተናግራለች፡፡ በየም ልዩ ወረዳ የባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የቱሪስት መስህብ ጥናት ባለሙያ አቶ በረከት ይገዙ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዕጸዋት የተለያዩ ክፍሎች የተለቀሙት ባህላዊ መድሃኒቶች ለሰው እና ለእንስሳት የሚሆኑት ተለይተው ይቀመጣሉ፡፡ የተለዩት መድኃኒቶችም  ከተቀሙ በኋላ በንጹህ ዕቃ  እንዲቀመጡ ተደርገው ህብረተሰቡ ለአንድ አመት እንደሚጠቀምበት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የጅማ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የኮፒ ራይትና የማህበረሰብ ዕውቅት ባለሙያ አቶ ኢብሳ ፊሌ " በየም ብሔረሰብ የሚካሄደው የባህላዊ መድሃኒት ለቀማ ሥነ ሥርዓት በማህበረሰብ እውቀትነቱ  በኢትዮጵያ አዕምራዊ ንብረት መመዝገቡ ህጋዊ የሚያደረገውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ አስተጽኦ አለው" ብለዋል፡፡ የየም ብሔረሰብን አገር በቀል እውቀት ፣ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የሚመለከተው  አካል ድጋፍ እንዲያደረግ በለቀማ ስነስረቱ ላይ ተጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም