ምክር ቤቱ "የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል" ለተባሉ ጉዳዮች ውሳኔ ሰጠ

117
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 የፌዴሬሽን ምክር ቤት "የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል" ተብለው በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጠ። ምክር ቤቱ አምስተኛው የፓርላማ ዘመን ሦስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሄዷል። የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ "የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል" በማለት ለምክር ቤቱ የተላኩና ለቋሚ ኮሚቴው ተመርተው አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎባቸው የውሳኔ ሃሳብ የቀረበላቸውን ጉዳዮች ተመልክቷል። ምክር ቤቱ ለውሳኔ ሃሳብ ከቀረቡ ከ20ዎቹ መካከል ቀደም ብሎ ለአስራ አንዱ ውሳኔ መስጠቱን አስታውሷል፤ የቀሩት ዘጠኝ ጉዳዮች ዛሬ ለውሳኔ ሃሳብ ቀርበዋል። በዚህም የውሳኔ ሃሳቦቹ ሲፈተሹ የእኩልነት፣ ፍትህ የማግኘት መብት፣ የንብረት መብትና ከመሬት ይዞታ ያለመነቀል መብት ጋር የተያያዙት ስድስት ጉዳዮች ላይ አጣሪ ጉባኤው የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። ምክር ቤቱም ሶስቱን ጉዳዮች በተመለከተ በሙሉ ድምፅ፣ ቀሪ ሶስት ጉዳዮችን ደግሞ በሰባት ተቃውሞ በስድስት ድምፀ ተአቅቦ አጽድቆታል። ቀሪዎቹን ሶስት ትርጉም የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ተጨማሪ ማጣራት እንዲካሄድባቸውና በቅርቡ ተጣርተው እንዲቀርቡ ወስኗል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ "የህገ-መንግስት ትርጉም አያስፈልጋቸውም" በማለት ውሳኔ የተሰጠባቸው 17 የይግባኝ አቤቱታዎችም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበዋል። ምክር ቤቱም የሙያተኞችን አስተያየት ካዳመጠ በኋላ ቋሚ ኮሚቴው መርምሮ "ትርጉም አያስፈልጋቸውም" በማለት የላካቸውን ውሳኔዎች  የህገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ውሳኔን በመደገፍ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቶ አፅድቆታል። እነዚህ ትርጉም አያስፈልጋቸውም የተባሉ የይግባኝ ጉዳዮች ከንብረት ክርክር፣ ከውል ስምምነት፣ ከመሬት ይዞታ መብት፣ ፍትህ የማግኘት መብት፣ ከካሳ ክፍያ፣ ከስርቆት፣ ከማታለል ወንጀልና  ከውርስ መብት ጋር የተያያዙ  የአቤቱታ ቅሬታዎች ናቸው። በተጨማሪም ምክር ቤቱ በማንነት ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል። በደቡብ ክልላዊ መንግስት፣ የብሔረሰቦች ምክር ቤት በደንጣ ማህበረሰብ የማንነት ጥያቄ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በተለያየ ቡድን በማደራጀት ቦታው ድረስ በመሄድ በህገ-መንግስቱ መሰረት ጥናት መደረጉ ተገልጿል። ቋሚ ኮሚቴው ሙያተኞች ያጠኑት ጥናት ሙያዊ አስተያየት ከህገ-መንግስቱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መስፈርት ጋር አነፃፅሮ የደንጣ ማህበረሰብ ተወካዮች ያቀረቡት "የማንነት መብት ይፈቀድልን" ጥያቄ "መስፈርቱን የሚያሟላ ሆኖ አልተገኘም" ሲል የቀረበውን ውሳኔ ሃሳብ አፅድቆታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም