ቤተክርስቲያኗ የምታከናውናቸውን የልማት ስራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

114
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ዘርፎች የምታከናውናቸውን የልማት ስራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች። በ31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ-ቅዱሳን ማርያም ገዳም የተገነባው ሁለገብ ህንፃ በዛሬው ዕለት ተመርቋል። የህንፃው ምረቃ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሌሎችም ብፁአን አባቶች ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት የቤተክርስቲያኗ የውጭ ግንኙነትና የአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት ኃላፊ ብፁእ አቡነ አረጋዊ እንደተናገሩት በቤተክርስቲያኗ ስር ያሉ አድባራትና ገዳማት በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች የልማት ስራዎችን አከናውነዋል። እየተደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ ነው ያሉት ብፁእ አቡነ አረጋዊ በቀጣይም አድባራቱና ገዳማቱ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። ቤተክርስቲያን ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በልማት ስራዎችም የምታከናውናቸውን ተግባራት አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል። ገዳማትና አድባራቱ ራሳቸውን ለመቻል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረው ይህ ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀው ስራ ነው ብለዋል። በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ-ቅዱሳን ማርያም ገዳም የተገነባው ህንፃም የገዳሟን አቅም የሚያጎለብትና ለተለያየ አገልግሎትና ለአገልጋይ ካህናት የሚውል ገቢ ከኪራይ ለማመንጨት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። የገዳሟ የልማት ኮሚቴ የምህንድስና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር በእምነት ጋሻው በበኩላቸው ህንፃው ከስድስት ዓመት በፊት መጀመሩን ገልፀው ለህንፃው ማሰሪያ የዋለው ገንዘብ ከገዳሟ እንዲሁም በተለያዩ የገቢ ማመንጫ ስራዎች የተገኘ መሆኑን አስታውቀዋል። ምዕመናን ህንፃው እስኪጠናቀቅ ድረስ በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነው በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ የሚኖሩ ምዕመናንም ቤተክርስቲያንን በመደገፍ ገንዘብ አመንጭታ ልጆቿን እንድትደግፍ ማስቻል ይገባቸዋል ብለዋል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በተገኙ ብፁአን አባቶች በቀጣይ ለሚሰራ ህንፃ የመሰረተ ድንጋይ ተጥሏል። አዲስ የሚገነባው ህንፃም ለአብነት ትምህርት ቤትና ለሰንበት ትምህርት ቤት የሚያገለግሉ ክፍሎች፣ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ፣ የቤተክርስቲያን ሙዚየም እንዲሁም ማየትና መስማት ለተሳናቸው ምዕመናን መማሪያና ለካህናት ማረፊያ የሚሆኑ ክፍሎችን ያካተተ እንደሚሆን ተገልጿል። ዛሬ የተመረቀው ህንፃ ባለ ስድስት ወለል ሲሆን የመኪና ማቆሚያን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ቢሮዎችንና የስብሰባ አዳራሾችን የያዘ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም