በክልሉ ለረጅም ጊዜያት መሬት አጥረው ወደ ስራ ባልገቡ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

62
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 በኦሮሚያ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ለረጅም ጊዜ መሬት አጥረው ባስቀመጡ  ባለሃብቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ300 ሄክታር በላይ መሬት መመለሱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። እንደኮሚሽኑ ገለጻ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማስመለስ ሂደትም ተጀምሯል። ኮሚሽነር ረሺድ ሙሃባ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለሀብቶች በወሰዱት መሬት በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ካልገቡ ኮሚሽኑ የድጋፍና ክትትል ስራውን ይሰራል ባለሀብቶችም ወደ ስራ እንዲገቡ በግፊት ጭምር ይደግፋል። ያ ሳይሆን ሲቀርና ከ6 ስድስት ወር በኋላም ወደ ስራ ካልገቡ ግን "መሬቱ ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ ይገባል" ብለዋል። ነገር ግን ባለሀብቶች መሬት በመውሰድ ሳያለሙ አጥሮ በሚያሰቀምጡበት ወቅት በኢኮኖሚ ላይም ክፍተኛ ጉዳት እንዳለውም በማውሳት። በክልሉ ኢንቨስተሮች በማኑፋክቸሪንግ፣ አግሮ  ፕሮሰሲንግ፣ ሜካናይዝድ  እርሻ፣ ኮንስትራክሽን፣ በሆቴል፣በቱሪዝም፣በግብርናና በሌሎች ዘርፎች ይሳተፋሉ። በዚህ ዓመት መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ በተመቻቸው ሁኔታ መሰረት በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራዎች በዚህ ዓመት በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት በማሳየት ላይ ይገኛሉ ተብሏል። የሚመጡት ኢንቨስትመንቶች ከኢንቨስትመንት አዋጭነት በተጨማሪ የሚፈጥሩት የስራ ዕድል፣ የሚያመጡት ካፒታል፣ የሚያካሄዱት የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር  እንዲሁም ከአየር ንብረት ተስማሚነታቸውና አካባቢን የማይበክሉ መሆናቸው ተረጋግጦ የሚሰጡ መሆናቸውንም አክለዋል። የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የመንገድ፣ የኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች በሚፈለገው ልክ የኢንቨስትመንቱ ስራ እንዳይሳለጥ እንዳደረገም አቶ ረሺድ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች 480 ፕሮጀክቶችን እንዲያለሙ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ እስካሁን ባለው መረጃም በሩብ ዓመቱ ከ6   ቢሊዮን ብር በላይ ላስመዘገቡ ኢንቨስተሮች ፈቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል ። ለዚህም በበጀት ዓመቱ ከ99 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ለባለሀብቶች የተዘጋጀ ሲሆን  ከ66 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ክልሉ ለማንኛውም የኢንቨስትመንት ስራ በጣም አመቺ በመሆኑ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሰማሩ ነው ኮሚሽነሩ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም