በከተማዋ 142 አዳዲስ የመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመዋል

137
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 በአዲስ አበባ ከ70 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው 142 አዳዲስ የመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች መገጠማቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ካሜራዎቹ ከሁለት ወር በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ታውቋል። የመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች በተለያየ የመሰረተ ልማት ግንባታ የተነሳ አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውንና መልሰው ወደስራ እንዲገቡ ለማስቻል ጥገና እየተደረገላቸው እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል። በኮሚሽኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዲቪዥን ተወካይ ምክትል ኢኒስፔክተር አንድነት ሲሳይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከተማዋ እያደገችና እየሰፋች መሆኗን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በተጨማሪም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ መጠን የተለያዩ ዜግነት ያላቸው ዜጎች ወደ ከተማዋ ለተለያዩ ስብሰባዎችና ኩነቶች የሚመጡባት በመሆኑ የደህንነት ጉዳዩን ማጠናከሩ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ ደህንነት ለማስጠበቅ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር እየተሰራ እንደሆነ ኢኒስፔክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም የጸጥታ አካላት የህብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅና የከተማዋን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ የተለያዩ የደህንነት ካሜራዎችን በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች መግጠም አስፈላጊ እንደሆነ የጠቆሙት ኢኒስፔክተር አንድነት በመጀመሪያው ዙር 142 አዳዲስና ዘመናዊ የመንገድ ላይ የደህንነት ካሜራዎች መገጠማቸውን አመልክተዋል። በዙሩ የተመረጠው አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለበት ሲሆን የውጭ አገር ዜጎች የሚበዙበትና ሰፊ እንቅስቃሴ ያለበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል። ካሜራዎቹ ሲገጠሙ የከተማዋን ውበት በማያበላሽ መልኩ እንዲሆን ለማስቻል ከአዲስ አበባ መንገዶች ጋር በመሆን በዲዛይንና መሰል ተግባራት በቅንጅት መሰራቱን ኢኒስፔክተር አንድነት አስታውሰዋል። ካሜራዎቹ የተገጠሙት በመብራትና በስልክ ፖሎች ላይ በመሆኑ ፖሎቹን በጋራ ለመጠቀምም ከመብራት ኃይልና ከኢቲዮ-ቴሌኮም ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር የካሜራዎቹን ትክክለኛ መረጃ አያያዝና ቴክኖሎጂ ዙሪያ በትብብር እንደተሰራ ገልጸዋል። ካሜራዎቹን የመግዛትና የመግጠም ስራው የተጀመረው 2008 ዓ.ም ሲሆን ስራው ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ አንጻር መዘግየቱን አንስተው የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ዝቅተኛ መሆን ስራውን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል። ''በተጨማሪም ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ የነበሩትን ሁሉንም ካሜራዎች በማስወገድ አዳዲስ ካሜራዎች የተገጠሙ በመሆኑ ስራውን ወደኋላ ጎትቶታል'' ብለዋል። በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ካሜራዎቹን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ የጠቆሙት ኢኒስፔክተር አንድነት በሁለተኛው ዙር ከእስጢፋኖስ አካባቢ በቤተ መንግስት አራት ኪሎን ጨምሮ መስቀል አደባባይ ላይ ካሜራዎች እንደሚገጠሙ ጠቁመዋል። ካሜራዎቹ በተገጠሙበት አካባቢ ደህንነታቸውን የመቆጣጠር ሃላፊነት የሁሉም ህብረተሰብ መሆኑን በመጠቆም ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ አሻራውን ማሳረፍ እንደሚገባው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።                                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም