'የሞጆ ደረቅ ወደብ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም' ተገልጋዮች

89
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ሲሉ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን ገለጹ። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ ወደቡ ባለበት የማሽን እጥረት ምክንያት ኮንቴይነርን ለጉምሩክ ፍተሻ የማቅረብ ስራ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ እየቀረበ መሆኑን አምኗል። የሞጆ ደረቅ ወደብ የአገሪቱ 80 በመቶ የገቢ ዕቃዎች የሚስተናገድበት ተርሚናል ነው። ገቢና ወጪ ኮንቴይነሮችን  ማራገፍና ለደንበኛ ማስረከብ፣ ጭነቶችን ወደ መጋዘንና ወደ ጉምሩክ ፍተሻ ቦታ የማድረስ አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ ለኢዜአ ቅሬታቸውን የገለጹ የደረቅ ወደቡ ተገልጋዮች  ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ ባለመሆኑ ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት መዳረጋቸውን ገልጸዋል። አቶ ሳምሶን አሰፋ ወደቡ የፎርክ ሊፍት  ችግር  ና የሰው ሀይል እጥረት በመኖሩ በወቅቱ መስተናገድ በሚገባን ጉዳይ ለጠጨማሪ  ቀናት መቆየት ና ክፍያ ተዳርገናል አብለዋል፡፡ አቶ አቡሽ ሰንደቁ እንዳሉት ለእግልትና አካላዊ ጉዳት መዳረጋቸውን ሲያስረዱ ''ብዙ መጉላላትና ብዙ ችግሮችን እያየሁ ነው።እኔ ራሱ ከማምሸቴ የተነሳ ፖሊስ መስለው ዘራፊዎች መንገድ ላይ ጠብቀው ደብድበውኝ ነበር።'' ''ለሊት ነው ጭነን የምንወጣው ችግር አለ እዛ ፍተሻውም ላይ ጉምሩክ በሰልፍ ነው የምንወጣው እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት ድረስ ቆይተን ነው የምንወጣው።'' የሚሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪአቶ ዳዊት ጥላዬ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ጉቱ እንዳሉት፤ ወደቡ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማሽኖች ያረጁና በቁጥርም አነስተኛ በመሆናቸው ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። አሁን በሥራ ላይ ያሉ ማሽኖች በሶስት ፈረቃ እንዲሰሩ እየተደረገ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ብልሽት ሲያጋጥማቸውም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ባለሙያዎችን በማስመጣት ጥገና እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በአገር ውስጥ ተመሳሳይ የደረቅ ወደብ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ባለመኖሩ ማሽኖችን በኪራይ ማግኘት አለመቻሉን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ችግሩን ለማቃለል ከድርጅቱ የጅቡቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተወሰኑ ማሽኖችን በማስመጣት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል። የደንበኞችን ፍላጎት ያሟላ አገልግሎት ለመስጠት የማሽን እጥረቱ አሁንም ያልተፈታ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል። ደረቅ ወደቡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ በተደጋጋሚ የተገልጋይ ቅሬታ የሚቀርበውን ኮንቴይነር ለጉምሩክ ፍተሻ የማቅረብ ስራ ላይ  እንደሆነም ተናግረዋል።  በደረቅ ወደቡ የማሽን ብልሽት ሲያጋጥመው ለተገልጋዩ የሚሰጠው አገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ከመውሰዱ ባለፈ ተገልጋዩ ተጨማሪ ክፍያ ይጠየቃል። ለአቶ ደሳለኝ 'የማሽኑ ብልሽት የደረቅ ወደቡ ችግር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደንበኞች አገልግሎት ማግኘት በሚገባቸው ጊዜ ሳያገኙ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቃቸው አግባብ ነው ወይ?' ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።  '' ለሚቆይበት ጊዜ እስካሁን ድረስ ያንን እንዳትከፍል የሚል መመሪያ የለንም።ነገር ግን ይሄን ጥያቄ ደንበኞቻችን አሁን ለኛም ያቀረቡልን ስለሆነ ዝም ብሎ ብቻ ደግሞ ክፍያ ማስቀረት አይቻልም።በነገራችን ላይ የኛ ታሪፍ በዚህ ድርጅት አይደለም የሚወሰነው የሚወሰነው በማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ነው። ብለዋል፡፡  የወደቡን የማሽን ችግር ለመፍታት በጊዜያዊነት እየተወሰዱ ካሉ መፍትሄዎች በተጨማሪ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር ዘመናዊ ማሽኖችን ለመግዛት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል። የሞጆ ደረቅ ወደብ በ30 ሄክታር መሬት ላይ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም