ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ 17 የኃይል ማመንጫና የመንገድ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች ሊገነቡ ነው

92
አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጭ 17 የኃይል ማመንጫና የመንገድ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ መወሰኑን የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት አስታወቀ። ቀደም ሲል በመንግስት ሲሰሩ የነበሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ ነው 17 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫና የመንገድ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ የተወሰነው። የግል ባለሀብቶች በመንግስትና በግል አጋርነት አሰራር መሰረት ፕሮጀክቶችን በራሳቸው ገንዘብና የሰው ኃይል በማልማት ከፕሮጀክቶቹ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ውሳኔው መንግስት የሚያወጣውን የገንዘብ ጫና ለመቀነስ፣ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና የጥራት ደረጃ እንዲሰሩ፣ የግሉ ዘርፍም ለአገር ግንባታ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ታምኖበት የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት(Public Private Prtinership) በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ተቋቁሟል። የአጋርነት ፕሮጀክቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተሾመ ታፈሰ እንደገለጹት፤ የመንግስትና የግል አጋርነት በቂ  ዝግጅት ከተደረገበትና የሕግ ማዕቀፍ ከተዘጋጀለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ እስከ አሁን የመንግስትና የግል አጋርነትን ለመተግበር ሙከራ ብታደርግም ሊለካ የሚችል ውጤት የተመዘገበበት እንዳልነበረ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመር የአገሪቱን ፖሊሲና ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ግዙፍ መሰረተ ልማቶችን ለመስራት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል ብለዋል። ከፕሮጀክት ልየታ ጀምሮ የጨረታ ሂደቱን የሚያጸድቅ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ ያሉበት ስምንት የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሁለት ልምድ ያላቸው የግል ባለሀብቶች የተካተቱበት ቦርድ መቋቋሙንም ገልጸዋል። በቦርዱ በመንግስትና በግል አጋርነት የሚሰሩ የመጀመሪያዎቹ 17 ፕሮጀክቶች የተለዩ ሲሆን 14ቱ ፕሮጀክቶች ከ3 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ ሦስቱ ደግሞ 357 ኪሎ ሜትር የአዳማ-ድሬዳዋ ፈጣን መንገድ ፕሮጀክቶች ናቸው። ገናሌ ዳዋ 5 እና 6፣ ጨሞጋ ያዳ፣ ወራቤሳ፣ ዳቡስ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ሲሆኑ ዲቸቶ፣ መቐለ፣ ሁመራ፣ ሁረሶ፣ መተማ፣ ወለንጭቲ፣ ጋድ፣ ወራንሶ ከፀሀይ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጭባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው። በውስጡ 18 ንዑስ ፕሮጀክቶችን የያዘ አንድ የኃይል ማሰራጫ ፕሮጀክትም በግል ባለሀብቶች እንደሚገነባ ያስረዱት ዶክተር ተሾመ ፕሮጀክቶቹ በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ መወሰኑን ተከትሎ በቅርቡ የጨረታ ሂደት እንደሚከናወን ተናግረዋል። ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የገንዘብና የቴክኒክ አቅም የሚጠይቁ ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማሳደግ በመንግስትና የግል አጋርነት አዋጅ መሰረት የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንና ሰራተኞችን ለሚያሳትፉ የውጭ ባለሀብቶች ለማበረታቻ ይካተታሉ ብለዋል። የግል ባለሀብቱ ፕሮጀክቶችን ከገነቡ በኋላ ቢያንስ ለ20 ዓመታት ከፕሮጀክቱ የሚገኘውን ገንዘብ እንዲወስዱ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል። የግል ባለሀብቱ አትራፊ እንደመሆናቸው መጠን ፕሮጀክቶችን ሲይዙ  በየጊዜው በሚፈጠር የገበያ መለዋወጥ በተጠቃሚው ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር በውሉ ላይ በአፅንኦት እንደሚሰራም ዶክተር ተሾመ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም