በምዕራብ ሸዋ ዞን በመጀመሪያው ዙር ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ይለማል

64
አምቦ ጥቅምት 17/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ዘንድሮ አመት በመጀመሪያው ዙር ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እንደሚለማ የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ገለጸ። በሁለት ዙሮች 100 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተክሌ ኢዶሳ ለኢዜአ እንዳሉት ልማቱ የሚካሄደው አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ በገበያ ተፈላጊ ምርቶች በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ነው። በልማቱ 32 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ይሳተፋሉ ከነዚህም ውስጥ በመጀመሪያው ዙር በሚካሄደው ልማት እስካሁን 7 ሺህ 563 ሄክታር መሬት በአትክልትና በበቆሎ ዘር መሸፈኑን ኃላፊው ገልጸዋል። ለልማቱ በአርሶ አደሩ ጉልበት የተዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብለዋል። በዞኑ በሁለት ዙሮች በመስኖ ከሚለማው 100 ሺህ ሄክታር መሬት 19ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ  አቶ ተክሌ አስታውቀዋል። ከመስኖ አልሚዎች መካከል የኤጀርሰለፎ ወረዳ  አርሶ አደር ታዬ ኦላና በሰጡት አስተያየት ገበያ ተኮር አትክልት በዓመት ሁለት ጊዜ በመስኖ በማልማት 140 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል።በትሩፋቱም የዘመናዊ መኖሪያ ቤት ባለቤት ሆነዋል። የጨሊያ ወረዳ  አርሶ አደር ቶለሳ ሁንዱማ በበኩላቸው መንግሥት በአካባቢያቸው ባስገነባው ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክት በመጠቀም አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ኑሮአቸው ተሻሽሏል። በየዓመቱ ከምርቱ ሽያጭ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙ የገለጹት አርሶ አደር፣በዚህም ኑሮአቸውን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት እንዳስቻላቸው ይናገራሉ። በመስኖ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ከ2006 ወዲህ በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት እስከ 130 ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶ ቤላማ ዱሜሳ ናቸው። በዘንድሮ የመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማትም በአንድ ሄክታር ይዞታቸው ላይ የጓሮ አትክልትና ቋሚ ተክል እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ባለፈው ዓመት በባህላዊና በዘመናዊ መስኖ ከለማው ከ93 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱ ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም