እይታቸው እስከ 10 አመታት ጠፍቶ የነበሩ ዜጎች በቀዶ ህክምና የዓይን ብርሃናቸው ተመለሰ

79
ደብረ ማርቆስ ጥቅምት 17/2011  እስከ አስር አመታት በሞራ ግርዶሽ ምክንያት ማየት ተስኗቸው  የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተደረገላቸው  ቀዶ ህክምና  የዓይን ብርሃናቸው ተመለሰ፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል በተደረገላቸው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና እይታቸው መመለሱን ነው ተጠቃሚዎች የተናገሩት፡፡ የእናርጅና እናውጋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ንጉሴ አካሌ ከ10 ዓመታት በፊት የዓይን ብርሃናቸውን አጥተው በመሪ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩበት ሁኔታ ወጥተው በሆስፒታሉ ሰሞኑን በተደረገላቸው ህክምና ሙሉ በሙሉ ለማየት በቅቻለሁ ብለዋል። የስናን ወረዳ  ነዋሪው አቶ ፋሌ አላምሬ እንዳሉት ለ4 ዓመታት ያህል ማየት ከልክሏቸው ቤት ውለው እንደነበር ያስታውሳሉ። እንቅስቃሴ ሳደርግ ጉድጓድ ውስጥ እየገባሁ ጉዳት ይደርስብኝ ነበርም በማለትም የዓይን በርሃናቸውን በማጣት የገጠማቸውን ያወሳሉ። በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ህክምና "የዓይን ብርሃኔን በማግኘቴ ዳግም የተወለድኩ ያህል ደሰማኛል" ብለዋል። ከአዊ ብሔረሰብ ዞን የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ያለምዘውድ መኩሪያ በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ህክምና ከ3 ዓመታት በፊት አጥተውት የነበረውን የዓይን ብርሃናቸውን መልሰው ማግኘታቸውን ይናገራሉ። በሆስፒታሉ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሰርጅን ወይዘሮ መቅደስ ዳኜ እንዳሉት ዳይሬክት ኤድ ከተባለ ድርጅት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር  የዓይን ግርዶሽ ችግር ላለባቸው ሰዎች የህክምና አገልግሎት ከጥቅምት 12-19/ 2011 በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በዚህም ሆስፒታሉ ኤድ ከተባለ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር  ነው ለ700 ሰዎች ህክምናውን የሰጠው። ህክምናው በመደበኛው ህክምና አሰጣጥ ረጅም ጊዜ የሚወስደውን አገልግሎት በተደራጀ አግባብ በአጭር ጊዜ በርካቶችን   ተጠቃሚ ለማድረግ ዓላማ እንዳለውም አብራርተዋል። በተጓዳኝም በትራኮማ ምክንያት እይታቸውን ላጡ ከ100 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች የዓይን ቆዳ መገልበጥ ህክምና እንደተደረገላቸው ወይዘሮ መቅደስ አስረድተዋል። በኢትዮጵያውያ የማየት ችግር ካለባቸው 1ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 600 ሺህ የሚሆኑት የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት በዓይን ሞራ ግርዶሽ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም