ተማሪዎች ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲማሩ ድጋፍ እናደርጋለን፤-የማይጨው ከተማ አገር ሽማግሌዎች

75
ማይጨው ጥቅምት 17/2011 በራያ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተማሪዎች ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲማሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የማይጨው ከተማ አገር ሽማግሌዎች ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በትምህርት ሚኒስቴር ዘንድሮ የተመደቡለትን  1 ሺህ 700 አዲስ ተማሪዎች ከጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም  ጀምሮ ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል። በዩኒቨርሲቲው የ2011 ዓ.ም የትምህርት መርሀ ግብርና የተማሪዎች አቀባበል ስነ-ስርዓት ላይ የሚመክር የአንድ ቀን የውይይት መድረክ ትላንት በማይጨው ከተማ ተካሄዷል፡፡ በመድረኩ ከተሳተፉ መካከል በማይጨው ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ አበበ ጓንጉል በዩኒቨርሰቲው የተመደቡ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከታተሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልጸዋል። "ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢም ሆነ በውጭ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሰላማቸው የተጠበቀ እንዲሆን የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል ። " ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች ከማይጨው ከተማ መናኽሪያ ጀምሮ አቀባበል ለማድረግ ተዘጋጅተናል " ያሉት ደግሞ ሌላው የአገር ሽማግሌ ሐጅ መሃመድ በርሄ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲተው የተማሪዎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማሟላት ለቅሬታ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮችን ቀድሞ ለማስገድ መስራት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ ገብረስላሴ ከበደ በበኩላቸው "ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎችን በመቀበል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የድርሻዬን እወጣለሁ" ብለዋል " የትግራይ ደቡባዊ ዞን ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተወካይ አዛዥ ኮማንደር ሐየሎም ማቸ በበኩላቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች ከከተማ መግቢያ ጀምሮ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጄኔ በበኩላቸው ተቋሙ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 1ሺህ 400 ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል። "ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮም የተመደቡለትን  1ሺህ 700 አዲስ ተማሪዎች ተቀብሎ ለማስተማር ተዘጋጅቷል" ብለዋል ። የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር የመምህራን ቅጥር፣ የቤተ-ሙከራ፣ የቤተ መጻህፍት፣ የመማሪያና የመኝታ አገልግሎቶችን የማደራጀትና የመሳሰሉ ሥራዎችን ማጠናቀቁን ለአብነት ጠቅሰዋል ። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል የሪፈራል ህክምና እንዲያገኙ ስምምነት መፈረሙንም ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።                                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም