የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ ጀምሮ በአሰላ ይካሄዳል

66
አሰላ ግንቦት 14/2010 በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚካፈሉ አትሌቶች የሚመረጡበት የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ይካሄዳል። ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከ100 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር የመም ውድድር፣ እርምጃና ሌሎች የሜዳ ላይ ተግባራት የሚደረጉ ይሆናል። በውድድሩ ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከ34 ክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ 624 ወንድና 474 ሴት በድምሩ 1 ሺህ 98 አትሌቶች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዚህ ውድድር አሸናፊ አትሌቶች በመጪው ሐምሌ 2010 ዓ.ም በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ በሚካሄደው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል። የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዕድሜቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች የሚካፈሉበት ሲሆን ውድድሩ ከ2004 ዓ.ም በፊት የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተብሎ ሲካሄድ ቆይቷል። ከአንደኛ እስከ ሶሰተኛ ደረጃን ይዘው ለሚያጠናቅቁ የሜዳሊያ ሽልማት እንዲሁም ለቡድን አሸናፊዎች ደግሞ የዋንጫ ሽልማት እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም