ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቤተሰባዊ ፍቅር በመስጠት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የበኩላችንን እገዛ እናደርጋለን - የከተማዋ ነዋሪዎች

43
ሰመራ ጥቅምት 16/2011 ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቤተሰባዊ ፍቅር በመስጠት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሎጊያ-ሰመራ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በሎጊያ ከተማ የሃይማኖት አባት ሽክ መሃመድ ሰኢድ በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች በዩኒቨርስቲውም ሆነ በከተማው በሚኖራቸው ቆይታ ደህንነታቸው ተጠብቆ ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ከዩኒቨርስቲው ባልተናነሰ የከተማው ነዋሪ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነዋሪው ተማሪዎችን እንደቤተሰቡና ልጆቹ በማየት አስፈላጊውን ድጋፋ በማድረግ መልካም ስም እንዳለውም ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም ይህን በጎ ተግባር የበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል ተማሪዎቹ ችግር እንዳይገጥማቸውና ላልተገቡ ሱሶችም ሆነ ሌሎች አደጋዎች እንዳይጋለጡ በመምክር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ''የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርስቲው የሚልኩት ዩኒቨርስቲውና የከተማው ህብረተሰብ የአባትና የእናትን ሚና እንዲወጣ አደራና ኃላፊነት በመስጠት ጭምር ነው'' ያሉት ደግሞ የሰመራ ከተማ የሃገር ሸማግሌ አቶ መሃመድ ሃሚድ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች በሚኖራቸው ቆይታ ያለምንም ችግር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ህብረተሰቡ እንደ ካሁን በፊቱ ሁሉ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው በማስተባበር ኃላፈነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል የስራ ሂደት አስተባባሪ ኮማንደር መሃመድ ኡትባን  ተማሪዎቹ በቆይታቸው ከህብረተሰቡ ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር ከዩኒቨርስቲው አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የጸጥታ ሃይሉም ከመቸውም ጊዜ በላይ ለተማሪዎች ደህንነትና ሰላም ትኩረት በመስጠት ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የዩቨርስቲው አምስተኛ አመት እንስሳት ህክምና ተማሪ አጥናፉ ረጋሳ በሰጠው አስተያየት ባለፉት አምስት ዓመታት ቆይታው ከዩኒቨርስቲ አስተዳደርም ሆነ ከከተማው ህብረተሰብ ጋር የነበረው ግንኙነት ሰላማዊና መልካም መግባባት የተሞላበት ነበር፡፡ በዚህ አመትም ከህብረተሰቡ የተደረገላቸው አቀባባል ይህን መልካም እሴት ጠብቆ ለማቆየት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያዩበት በመሆኑ ትምህርቱን ያለምንም ስጋት ተረጋግቶ ለመቀጠል መነሳሳት እንደፈጠረበት ተናግሯል፡፡ እሱም በዩኒቨርስቲው በሚኖረው ቆይታ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ተሞክሮውን በማካፈል እንዲሁም ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ከጎደኞቹ ጋር በመንቀሳቀስ ግጭትም ሆነ ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት እንደሚጠነቀቅ ተናግሯል፡፡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አደም ቦሬ እንደገለፁት ዩኒቨርስቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ባህሉ ይታወቃል፤ ይህን ጠንካራ ባህል አጠናክሮ ለመቀጠል ከሃይማኖት አባቶችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተቀራርቦ እየተሰራ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው ከ4ሺህ በላይ ነባር ተማሪዎቹን በሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ እየተቀበለ ሲሆን ተማሪዎቹ በሚገቡባቸው አራት ዋና ዋና በሮች ለተማሪዎቹ አቀባባል መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከጥቅምት 19 እስከ 20 2011 ድረስ ደግሞ ከ3ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል የተማሪዎች ህብረት አባላት አቀባበልና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን እንዲያመቻቹ መመደባቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የተማሪዎች ካፌ፣ ማደሪያና ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክፍተቶችን  በመቅረፍ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ደስተኛ ሆነው እንዲከታተሉ ዝግጅት መደረጉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም