በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወጣቶች ይሳተፋሉ

46
አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ አምስት መቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት የበጋ ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚከናወን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አምስት ነጥን አምስት ሚሊዮን ወጣቶች ይሳተፋሉ። በየዓመቱ በክረምትና በበጋ ወቅት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ሲሆን፤ በአገልግሎቱም ኀብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ከሚሰጡት አገልግሎቶች ውስጥ የማስተማር፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ልማትና ችግኝ ተከላ እንዲሁም የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ይጠቀሳሉ። እንዲሁም የጎዳና ወጣቶች የስራ ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸትና ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ፣ አረጋዊያንን መርዳት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት፣ በአገር ሰላምና አንድነት ላይ ውይይት ማካሄድ በወጣቶቹ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ማካተት፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ማትያስ አሰፋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በክረምት ወራት ሲከናወን የቆየው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወቅትም ቀጣይነት አለው። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አገልገሎቱ በይፋ መጀመሩን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማይቋረጥ እንደሆነም ገልጸዋል። በበጋ ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት የሰብል መሰብሰብ እገዛን ጨምሮ የማህበራዊ አገልግሎትና የጤናው ዘርፍ ላይ በተመሳሳይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ዓመቱን ሙሉ መሰጠቱ የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከርና ዜጎች የባህል ልውውጥ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። አገልግሎቱ የተለመደና ባህል እየሆነ በመምጣቱ የሚያስገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስቀጠል እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው ያመለከቱት። የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አብረሃም ኤርዳ እንደገለጸው፤ በበጋ ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ447 ሺ በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል። በክረምት ወቅት የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋ ወቅት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ የከተማዋ ወጣቶች ባላቸው ትርፍ ጊዜ የአገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክረምት ወቅት ብቻ የሚከናወን ተግባር እንዳይሆን እና ዜጎች አገልግሎቱን ባህል አድርገው እንዲወስዱት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። በመዲናዋ ባሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች የትራፊክ ደህንነት፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጥበቃና ጽዳት፣ የተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርትና ሰብዓዊ አገልገሎት ዓመቱን ሙሉ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው። ተቋማት በክረምት ወቅት ሲደርጉ የነበረውን ድጋፍና ክትትል በበጋው ወቅትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል። ባለፈው በጀት ዓመት በመዲናዋ ወጣቶች በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 23 ሚሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለ የገለጸው ወጣት አብርሃም፤ ዘንድሮ ደግሞ 27 ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ ለማዳን መታቀዱን ገልጿል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ የሚፈልግ ሰው በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት በመገኘትና በሚፈልገው የሙያ መስክ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ጠቁሟል። ባለፈው የክረምት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘጠኝ ሚሊዮን ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም