የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታቸው የልማት ተነሳሽነታቸውን እንዳጎለበተው የዳኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ

162
አምቦ ጥቅምት 16/2011 የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታችን ለይዞታችን ዋስትና ከመሆን ባለፈ የልማት ተነሳሽነታችንን አጎልብቶታል ሲሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን የዳኖ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። የወረዳው የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጽህፈት ቤት በበኩሉ በዚህ ወር ከ10 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡ አየወረዳው አርሶ አደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  እንደገለጹት ካርታው በወሰን መገፋፋት ምክንያት ይከሰት የነበረውን አለመግባባት ይፈታል።ለልማት ያላቸውን ተነሳሽነትም አሳድጎታል። በየድሬ ሃረዩ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር በሻዳ ጉዲሣ ከዚህ ቀደም መሬታቸው በባህላዊ መንገድ ተለክቶ ስለተሰጣቸው ከአጎራባቻቸው ጋር በወሰን ይገባኛል ሲጋጩ ቆይተዋል። ለሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ይዞታቸው ማረጋገጫ ካርታ ማግኘታቸው የራሳቸውን ይዞታ ለይተው እንዲያውቁ ከማድረጉም በላይ ያጋጥማቸው የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት አስችሎናል ብለዋል፡፡ ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የአንጨቢ በዴሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጂቱ ደለሊ ከዚህ ቀደም ከባለቤታቸው ጋር በነበራቸው የፍርድ ቤት ክስ ለተወሰነላቸው አንድ ነጥብ አምስት ሄክታር  መሬት ካርታ ማግኘታቸው አስደስቷቸዋል። ማሳቸውን ህጋዊ የሚያደርግላቸው ካርታ መሬታቸውን አከራይተውም ሆነ አልምተው ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን የዳኖ ወረዳ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለማ ድሪቢ በበኩላቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ለአርሶ አደሮች መስጠቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ በወረዳው በስፋት ይታይ የነበረውን የወሰን መገፋፋትና በዚህም ምክንያት የሚመጣውን አለመግባባት ያስቀራል ብለዋል። ሴቶችም ከወንዶች እኩል ባለመብት መሆናቸውን የሚያረጋግጡበትና ምርትና ምርታማነትንም ለመጨመር ያስችላል፡፡ በወረዳው 46 ሺህ ሄክታር መሬት ባለይዞታ ለሆኑት 10 ሺህ 114 አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን አስታውቀዋል።ከነዚህም  1  1 ሺህ 620 ሴቶች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም