ሠራተኞቹ ምደባው የትምህርት ዝግጅትንና የሥራ ልምድን መሠረት ያላደረገና ፍትሃዊነት የጎደለው ነው …የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች

46
ደብረ ማርቆስ ጥቅምት 15/2011 የትምህርት ዝግጅትንና የሥራ ልምድን መሠረት ያላደረገው ምደባ ፍትሃዊነት የጎደለውና የመሥራት ፍላጎታችንን ጎድቶታል ሲሉ የደብረ ማርቆስ  ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ቅሬታቸውን አሰሙ። ዩኒቨርሲቲው ምደባው የሠራተኞችና መመሪያና ደንብን መሠረት በማድረግ በጥራት ተከናውኗል ይላል። ምደባው ሥራንና ሠራተኛን በልምድም ይሁን በትምህርት ዝግጅት ያላገናኘና ጥናት የጎደለው በመሆኑ ሊስተካከል ይገባዋል ብለዋል። ቅሬታ አቅራቢ ሠራተኞች ለኢዜአ እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው ያደረገው ምደባ ወጥ የሆነ አሰራር ያልተከተለና ኢፍትሃዊ ነው። አቶ ዘላለም አዱኛ የተባሉ ሠራተኛ በሒሳብ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪና ከአምስት ዓመት በላይ አገልግሎት ይዘው በፊት ይሰሩበት ከነበረው ደረጃ በአራት ዝቅ ብለው  በጥበቃ ሙያ መመደባቸው አግባብ አለመሆኑን ይናገራሉ። ይህም የሥራ መነሳሳት እንዳሳጣቸው ገልጸዋል። አቶ ይታያል የኔአለም የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ኢፍትሃዊ  ምደባ ማድረጉን ይገልጻሉ። በማኔጅመንት ዲግሪ ቢኖራቸውም ከተማሪዎች ሞግዚትነት ተነስተው ወደ አትክልተኝነት ዝቅ ተደርጌ ተመድቤያለሁ ብለዋል። በተጨማሪም ማኔጅመንት ለሚፈልገው የሥራ መደብ በአማርኛና ባዮሎጂ ትምህርት ምሩቃን መመደባቸውን ገልጸዋል።መዳቢው አካል ለዚህ  የአገልግሎት ርዝማኔን በምክንያትነት እንደሚያቀርብም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ምደባ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ያላስጠበቀና በዘፈቀደ የተሰራ ነው ያሉት ደግሞ አቶ ሰፊነው አየልኝ የተባሉ ሠራተኛ ናቸው። እሳቸው በአፕላይድ ሲቪክስ የመጀመሪያ ዲግሪና የስድስት ዓመት አገልግሎት ይዘው ከተማሪዎች ሞግዚትነት ወደ አትክልተኛ ሲመደቡ 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ሠራተኞች ደግሞ በሞግዚት መመደባቸውን ይገልጻሉ። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው  ከ1 ሺህ 370 በላይ ለሆኑት ሠራተኞች ምደባ ለማከናወን ኮሚቴ አቋቁሞ መመሪያውን ተከትሎ መሥራቱን አስታውቀዋል። በዚህም ከ1 ሺህ 45 በላይ ሠራተኞች በአንደኛና ሁለተኛ ምርጫቸው መመደባቸውን ይገልጻሉ። ከ100 በላይ የሚሆኑት በትይዩ የሥራ መደብ ሲስተናገዱ፣መስፈርት ያላሟሉ ከ100 በላይ ሠራተኞች ዝቅ ብለው መመደባቸውን  አብራርተዋል። ምደባው በኢፍትሃዊነት እንዳልተከናወነ የሚናገሩት ዶክተር ታፈረ፣መመሪያው ሠራተኞች ይሰሩበት የነበረው መደብ የመጀመሪያ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ ስለማይል የ10ኛ ክፍል ያጠናቀቁት ተመድበዋል ብለዋል። በዚህም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘው በተማሪዎች ሞግዚትነት ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞች ወደ ጥበቃና አትክልተኝነት የ10ኛ ክፍል የትምሀርት ማስረጃ ይዘው የተቀጠሩ ደግሞ የጥበቃ ሠራተኛ፣ የተላላኪነና የአትክልተኛ መደቦች  መያዛቸውን ተናግረዋል። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ጨምሮ ከሁለት ሺህ በላይ ሠራተኞች አሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም