ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር እስከ ውህደት የሚዘልቅ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

194
አዲስ አበባ ጥቀምት 15/2011  ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር የተሰኙት የፖለቲካ ድርጅቶች እስከ ውህደት የሚዘልቅ  ትብብር ለመፍጠር ተስማሙ። ፓርቲዎቹ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ ውህደት መፍጠር በሚችሉበት መንገድ ላይ ተከታታይ ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በቅርቡ ወደአገር ቤት ከተመለሱት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ፓርቲው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደአገር ቤት ከመጣ ወዲህ የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት እስከ ውህደት የሚደርስ ትስስር ለመፍጠር ከዓረና ትግራይ ጋር ሲመካከር መቆየቱንና በወሳኝ ፖሊሲዎች ላይም ከስምምነት መድረሳቸውን በመግለጫው ይፋ አድርገዋል። ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር መምህር ጎይተኦም ፀጋይ ፓርቲዎቹ የአገሪቱ የምርጫ ህጎችን ተከትለው እስኪወሃዱ ድረስ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸውን በጋራ ለማድረግ መስማማታቸውን አመልክተዋል። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግደይ ዘርአጽዮን በበኩላቸው እንደገለፁት በሁለቱ  ድርጅቶች መካከል የዓላማና የፖሊሲ ልዩነት የለም። ድርጅቶቹ ወደፊት ተዋህደው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸው ለትግራይ ህዝብ ተስፋ ሰጪ ነው ያሉት አቶ ግደይ ውህደቱ በአጭር ጊዜ እንዲሳካ ድርጅታቸው ህጋዊ ሰውነት የሚያገኝበትን ተግባር እንደሚያከናውን ተናግረዋል።  ድርጅቶቹ ተዋህደው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ የደረሱት ስምምነት በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተዋህደው ጠንካራ ድርጅት ለመፍጠር መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን አቶ ግደይ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም