የትግራይ አርሶ አደሮች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት እንዲሰበስቡ ተጠቆመ

55
መቀሌ ጥቅምት 15/2011 የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ርብርብ በማድረግ እንዲሰበስቡ የክልሉ ግብርና ገጠር ልማት ቢሮ አስገነዘበ። የቢሮው የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ምሩፅ ዛሬ እንዳሳሰቡት አርሶ አደሮቹ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ዝናብ  የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ ጉልበታቸውን አስተባብረው መሰብሰብ አለባቸው። አርሶ አደሮቹ ሰብሎች ባልተጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ የግብርና ባሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክር እንዲተገብሩም ጠይቀዋል። በእንደርታ ወረዳ የለምለም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መሓሪ ፀጋይ ሰብላቸው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት በማጨድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በወረዳው በአራጉረ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ኃይሉ ፀጋይ በበኩላቸው፣ዝናቡ በዋናነት ጤፍን ስለሚያረግፍ ከአካባቢዬ አርሶ አደሮች ጋር ተቀናጅተን እየሰበሰብን ነው ብለዋል። በክልሉ በ2010/11 የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም