የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችን የሚያስወግደው ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ነው- የሆስፒታሉ ሃኪሞች

124
ባህር ዳር ጥቅምት 15/2011 የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድሃኒቶች ጨምሮ ሌሎች ቆሻሻዎችን ሳይንሳዊ  ባልሆነ ሁኔታ በግቢው ውስጥ የሚያስወገድበት መንገድ ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጠናል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የሆስፒታሉ ሀኪሞች ገለጹ። ቆሻሻውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማስወገድ ከከተማ አስተዳደሩ ቦታ ማግኘት ባለመቻሌ ችግሩ አስከፊ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል ሲል ሆስፒታሉ አስታውቋል። የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ሱፌ ሙሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ከሆስፒታሉ የሚወገዱት ለህክምና አገልግሎት ተበለው የሚገዙ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የካንሰር መድሃኒቶችን ጨምሮ ሌሎችም መድሃኒቶች ናቸው። ለፈውስ አገልግሎት ይውላሉ ተብለው የተቀመሙ መድሃኒቶች አገልግሎታቸው ሲያልፍ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ካልተወገዱ ይፈውሱታል ተብለው ለተቀመሙለት በሽታ ዞረው መንስኤ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የቆሻሻ አወጋገድ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶች የሚያደርሱትን ጉዳት ከግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ ህሙማን ተኝተው በሚታከሙበት አልጋ ክፍሎች አጠገብ ይቃጠላል፡፡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ  ሳይንሳዊ ያልሆነና ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በፍጥነት መፍትሄ ሊሰጠው  ይገባል በሚል ከሀኪሞቹ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለሆስፒታሉ ቢቀርብም መፍትሄ ማግኘት አልመቻሉን ዶክተር ሱፌ ተናግረዋል፡፡ መድሃኒቶች በባዶ ሜዳ ላይ በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ  በመቃጠላቸው ጭሱ ለመዳን የመጣውን ታካሚ ለተጨማሪ በሽታ የሚዳርግ  መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ሱፌ ” እኛም ስለ ታካሚዎች  ከማሰብ ይልቅ ለራሳችን ደህንነት በመስጋት ላይ ነን” ብለዋል፡፡ ዶክተር ሰርካለም ዘውዴ በበኩላቸው የሆስፒታሉ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት  ሳይንሳዊ ያልሆነና ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ የሆስፒታሉን ታካሚም ሆነ የከተማውን ነዋሪ  የበሽታ ተጠቂ እያደረገው  መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ ከሆስፒታሉ ማህበረሰብ ስጋት ባለፈ በጭሱ አማካኝነት ሊፈጠር የሚችል በሽታ ለከተማው ነዋሪ  አደገኛ ነው ሲሉ አብራርተዋል። ሆስፒታሉ ችግሩን በፍጥነት ማስተካከል ሲገባው የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ችግሩ አስከፊ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረጉን ተናግረዋል። የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ ባየ  ችግሩ አስከፊ ከሚባልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተናግረው፣"ቆሻሻን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማስወገድ የሚያስችል ቦታ ሆስፒታሉ ስለሌለው ችግሩ ሊባባስ ችሏል" ብለዋል። ለሆስፒታሉ ቆሻሻ ማስወገጃ የሚሆን  ከከተማው ወጣ ያለ ቦታ የባህርዳር ከተማ ማዘጋጃ ቤት እንዲሰጥ  በተደጋጋሚ የተጠየቀ ቢሆንም ሆስፒታሉ ለቦታው ካሳ መክፈል አለበት የሚል ምላሽ መሰጠቱንም ገልጸዋል። የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ማመቻቸት የከተማው ማዘጋጃ ቤት መሆኑን የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ  ሆስፒታሉን  ካሳ መጠየቅ አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመው፤  ሆሰፒታሉ ካሳ የመክፈል አቅም ስለሌለው የከተማው ማዘጋጃ ቤት የቆሻሻ ማስወገጃ  ቦታ ሊያመቻች ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል። ይህ ካልሆነም  ችግሩ ተባብሶ  እንደሚቀጥል  ሜዲካል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር  ከህክምና ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎች የሚወገዱት በራሳቸው በህክምና ተቋማት በመሆኑ ሆስፒታሉ በራሱ አቅም ችግሩን ሊፈታ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳትና ውበት ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት የኔው  "የጤና ተቋማት የቆሻሻ አወጋገድ የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ መመሪያ ስላለው ከከተማ አስተዳደሩ ጋራ የሚያገናኝ ምንም አይነት ምክንያት የለውም" ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩ አደገኛ ያልሆኑና አካባቢን ሊያቆሽሹ ይችላሉ የተባሉ ከንግድና መስል ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎችን የማስወገድ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ አደገኛ የሚባሉና በሰውና በእንስሳት ላይ የከፋ የጤና ችግር ሊያደርሱ የሚችሉ  ከጤና ተቋማት የሚወጡ ቆሻሻዎች የሚወገዱት በራሳቸው በጤና ተቋማት አማካኝነት እንደሆነም ኃላፊው አስታውቀዋል። ለቆሻሻ ማስወገጃ የሚሆን ቦታ ለማግኘት ካሳ የመክፈል ግዴታ የጤና ተቋማት እንደሆነ አቶ ዳዊት ገልጸዋል። ሆስፒታሉ በራሱ የአስተዳደር  ጉድለት  ምክንያት ችግሩን የሌላ አካል ማድረግ እንደሌለበት የጠቆሙት ኃላፊው   ሆስፒታሉ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል። የኢዜአ ሪፖርተር በቦታው ላይ በነበረው ቅኝት የፈለገ-ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የቆሻሻ አወጋገድ  መድሃኒቶች የሚያደርሱትን ጉዳት ከግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ ህሙማን ተኝተው በሚታከሙበት አልጋ ክፍሎች አጠገብ  በማቃጠል እንደሚከናወን  ተመልክቷል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም