የዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተያዘላቸው የበጀት መጠንና የጊዜ ገደብ እየተፈፀሙ አይደለም

67
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በመንግስት ወጪ የሚሰሩ ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በተያዘላቸው በጀትና የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቁ አለመሆኑን የኮንትራክሽን ዘርፍ ትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አስታወቀ። ብዙዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ትክክለኛ የጨረታ ሂደት እንደማይከተሉም ተጠቅሷል። ተቋሙ በመንግስት በጀት የሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች ያለምንም ጥያቄ መረጃዎቻቸውን ለህዝብና ለሚመለከተው የመንግስት አካል ይፋ የማድረግ ስራ የሚሰራ ነው። የተቋሙ የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ያለው እንደተናገሩት፤ በአምስት ዙር ተለይተው ስልጠና ከተሰጣቸው 32 ዩኒቨርሲቲዎች 15ቱ የፕሮጀክት አፈፃፀም መረጃቸውን በመንግስት ግዢ ድረገፅ ይፋ ማድረግ ቢችሉም የተቀሩት 17 ዩኒቨርሲቲዎች ግን መረጃ ለመስጠትም ሆነ አፈፃፀማቸውን ለማሳወቅ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። መረጃቸውን ይፋ ካደረጉ 2 ካላደረጉ ደግሞ 7 ተመርጠው በ9 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በተካሄደ ዳሰሳ አብዛኞቹ ትክክለኛ የጨረታ ሂደቶችን የማይከተሉ፣ በተያዘላቸው በጀትና የጊዜ ገደብ የማይፈፀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። የዳሰሳ ጥናቱ የተካሄደባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መረጃ እንደሚያሳየውም ጨረታቸው ውስን የሆኑ፤ ቅድመ ጥናት ያልተደረገባቸው መሆናቸውን ያሳያል። በጥናቱ ከቀረቡት መካከል የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ህንፃ ግንባታን ለማከናወን 181 ሚሊዮን 735 ሺህ ብር ቢያዝለትም ተጨማሪ 14 ሚሊዮን 543 ሺህ ብር ወስዷል። ከዚህ በተጨማሪም በሁለት አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ውል ቢገባም ግንባታው አምስት አመታትን ፈጅቷል። በተመሳሳይ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የመኝታ፣ የመማሪያ ክፍሎችና የካፍቴሪያ ግንባታ ከታየዘላቸው በጀት ተጨማሪ 12 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን ከአንድ አመት በላይ የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ ፈጅተዋል። ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ አዲስ አበባ፣ ወሎ፣ አክሱም፣ ደብረታቦርና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው መሆኑን ነው የዳሰሳ ጥናቱ የሚያሳየው። ስልጠናውን ወስደው መረጃዎቻቸውን ይፋ ካላደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ የግንባታ ፕሮጀክት የሚፈፅሙ የፌዴራል ተቋማትም እንደሚገኙበት አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። በመንግስት ግዢ አስተዳደር ተለይተው ስልጠና ከወሰዱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና የመንግስት ቤቶች አስተዳደር መረጃቸውን ይፋ ሲያደርጉ የፌደራል ፖሊስ፣ አየር መንገድ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የቀድሞ ወጣቶችና ስፖርት መረጃቸውን ይፋ ለማድረግ ተባባሪ አልሆኑም ብለዋል። እንጠየቃለን የሚል ፍርሃት፣ ስጋትና የመረጃዎች አያያዝ ግድፈት መረጃዎችን ለህዝብና ለመንግስት ይፋ ላለማድረጋቸው ምክንያት እንደሆነም ነው ስራ አስኪያጁ የገለፁት። ተቋሙ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ በ52 የመንገድ፣ የውሃና የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች ባደረገው ጥናት ፕሮጀክቶቹ ከተያዘላቸው የገንዘብና የጊዜ በጀት በላይ የሚወስዱ መሆኑን መለየቱን አስታውቋል። እንደአጠቃላይ ከነዚህ ውስጥ የውሃ ፕሮጀክቶች ከእጥፍ በላይ ተጨማሪ ወጪን የጠየቁ ሲሆን በመንገድም ከ41 በመቶ በላይ ተጨማሪ ገንዘብ የጠየቁ ነበሩ ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም