በምዕራብ ወለጋ ዞን በመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት እንቅስቃሴ 45 ሺህ ሄክታር መሬት ይለማል

65
ጊምቢ ጥቅምት 15/2011 በምራብ ወለጋ ዞን በመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት እንቅስቃሴ 45 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የዞኑ መስኖ ልማት ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት ኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሐብቴ ዋቅጅራ እንደተናገሩት በባህላዊና በዘመናዊ መንገዶች ልማቱ የሚካሄደው ልማት በ20 ወረዳዎች ነው። ከመስከረም ወር ወዲህ እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴም 1 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ታርሶና ለስልሶ በዘር ተሸፍኗል። ልማቱን በበቆሎ፣ በማሽላ፣በቅመማ ቅመም እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። በልማቱ 10 ሺህ ሴቶችን ጨምሮ 60 ሺህ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሐብቴ፣ በልማቱም አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። ጽህፈት ቤቱ በዞኑ ልማቱን ለማስፋፋት እያጋጠመ ያለውን የውሃ መሳቢያ ሞተሮች እጥረት ለማቃለል በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ አካላት ጋር  እየተነጋገረ መሆኑንም ገልጸዋል። ከመስኖ አልሚዎች መካከል የነጆ ወረዳ ቢቅልቱ ዲላ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ንጋቱ ለቴራ በባህላዊ መስኖ የሚያመርቱትን አትክልት ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል። ዓምና በመስኖ ካለሙት ግማሽ ሄክታር መሬት ከ80 ኩንታል በላይ ቲማቲምና ቃሪያ ሸጠው 20 ሺህ ብር ትርፍ አግኝተዋል።ዘንድሮም በተመሳሳይ መሬት ላይ ልማቱን እያካሄዱ ይገኛሉ። የቂልጡ ካራ ወረዳ ለሊሳ ከሚሳ ቀበሌው አርሶ አደር ዱጋሳ ሞሲሳ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ሩብ ሄክታር መሬት መስኖ አልምተው ከ30 ኩንታል በላይ ነጭ ሽንኩርት ማግኘታቸውን ይናገራሉ። ዘንድሮ ደግሞ ምርታቸውን 40 ኩንታል ለማድረስ  እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በየዓመቱ በቆሎ፣ ድንች፣ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን በባህላዊ መስኖ በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ በወረዳው የወንዲ ዳሌ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋ ለታ ናቸው። በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው መሬት 124 ሚለዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም