የእምቦጭ አረምን ማጽዳት የሚያስችል ጀልባ መስራቱን የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አስታወቀ

80
አርባ ምንጭ ግንቦት 14/2010 በአባያ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ማጽዳት የሚያስችል ዘመናዊ ጀልባ መስራቱን የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አስታወቀ። ጀልባው በአንድ ቀን 10 ሺህ ቶን የእምቦጭ አረምን አጭዶ የመፍጨት አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን በሐይቁ ላይ ሙከራ ተደርጎ ውጤታማነቱም ተረጋግጧል። የኮሌጁ ምክትል ዲንና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ኃይለሚካኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት እምቦጭ አረምን በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ከአባያ ሐይቅ ለማጽዳት የሚደረገውን ዘመቻ ለማገዝ ጀልባው የጎላ ጠቀሜታ አለው። ጀልባው አቶ መኮንን ፍላቴ በተባሉ የኮሌጁ መምህር አስተባባሪነትና በሌሎች አራት የኮሌጁ አሰልጣኞች የተሰራ መሆኑንም አቶ ወርቅነህ ገልጸዋል። ጀልባው ከአባያ ሐይቅ ላይ አረሙን ከማጽዳት በተጨማሪ በአባያና ጫሞ ሐይቆች ለትራንስፖርትና መዝናኛ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት። በዚህም በአባያ ሐይቅ ላይ ከዚህ በፊት ተጀምሮ የተቋረጠውን ከአርባ ምንጭ ዲላ የውሃ ላይ ትራንስፖርት ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። "የትራንስፖርቱ አገልግሎት ሲጀመር ከአርባ ምንጭ ዲላ በየብስ ጉዞ ይፈጅ የነበረውን የአስር ሰዓት መንገድ በ45 ደቂቃ መድረስ ያስችላል" ብለዋል፡፡ በጫሞ ሐይቅ በሚገኘው ጋንጁላ ደሴት ላይ ለሙሽሮች ሽርሽርና ለቱሪስት መዝናኛ የሚውል ተመሳሳይ ጀልባም በቅርቡ ሰርቶ በማህበር ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ለማሸጋገር እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ የሚገኘው አርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከ28 በላይ ቴክኖሎጂዎችን በመኮረጅ ለሕብረተሰቡ ማሸጋገሩን ከኮሌጁ የተገኘ መረጃ ያሳያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም