የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ምርቶች ይዘው የተገኙ የሸማቾች ማህበር ሱቆች እርምጃ ተወሰደባቸው

96
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ የምግብና የጽዳት መጠበቂያ ምርቶች የተገኘባቸው የሸማቾች ማህበር ሱቆች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት 'ብርሃን ለሕዝብ ሸማቾች የሕብረት ስራ ማህበር' አራት ሱቆች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የምግብና የጽዳት መጠበቂያ ምርቶች ይዘው በመገኘታቸው እንዲታሸጉ ተደርጓል። ቢሮው ከሕብረተሰቡ የተገኘውን ጥቆማ  በማጣራት እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል። እንደ አቶ መስፍን ገለጻ የማህበሩ አመራሮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ምርቶች መኖራቸውን እያወቁ ለማስወገድ ጥረት ባለማድረጋቸው በህግ ይጠየቃሉ። የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ካለፈባቸው ምርቶች መካከል ማጂ መረቅ፣ ኢንዶሚ የህጻናት ምግብ፣ ላርጎ ፈሳሽ ሳሙና፣ ቬራ ፓስታ፣ ሳልሳ፣ የልብስ ሳሙናና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። አቶ መስፍን እንደገለጹት የማህበሩ ሱቆች ታሽገው የቆዩ ሲሆን የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች ከተወገዱ በኋላ እንዲከፈቱ ተደርጓል። ሕብረተሰቡ በየትኛውም ቦታ በሚገበያይበት ወቅት የምርቶችን የመጠቀሚያ ጊዜ በትኩረት ማየት እንደሚገባውና ጊዜያቸው ያለፈ ምርቶች ሲያጋጥሙት ለቢሮው ጥቆማ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የአራዳ ክፍለ ከተማ የንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃብታሙ ደሳለኝ በማህበሩ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች የተገኙበት ከሕዝብ ደህንነት ይልቅ የግለሰብን ጥቅም በማስቀደም መሆኑን ተናግረዋል ። በንግድ ቢሮ ሬጉላቶሪና ኢንስፔክሽን መመሪያ መሰረት ማህበሩ የምርቶች የመጠቀሚያ ጊዜ የሚያልፍበት ወቅት ሶስት ወር ሲቀረው ምርቶቹን ቆጥረው ለንግድ ጽህፈት ቤት ማሳወቅ ሲገባቸው አለማሳወቃቸውን ተናግረዋል። በክፍለ ከተማው የሚገኘው የሕብረት ስራ ማህበራት ቢሮ ከግንቦት ወር ጀምሮ ለማህበሩ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ጊዜያቸው የተቃረቡ ምርቶችን እንዲያስወግዱ የጽሁፍና የቃል ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ምርቶቹን አለማስወገዳቸውን አቶ ኃብታሙ አንስተዋል። እነዚህ ምርቶች ለሕብረተሰቡ ለሽያጭ ላለመቅረባቸው ማረጋገጫ አለመኖሩንም ጠቁመዋል። የሸማቾች ማህበራት የህዝብ ተቋማት ናቸው የሚል አመኔታ መኖሩና ሌላ የንግድ ተቋም ላይ በሚደረገው መልኩ ክትትልና ቁጥጥር እንዳልነበረም ተናግረዋል።። በቀጣይም በሸማቾች ማህበራት ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚጠናከር ነው የገለጹት። በክፍለከተማው ወረዳ አራት ብርሃን ለሕዝብ ሸማቾች የሕብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ በለጠ ጥሩነህ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶች ተለይተው የተቀመጡ እንጂ ለሽያጭ የቀረቡ አይደሉም ይላሉ። ምርቶቹ ከዩኒየኖች የሚቀርቡ መሰረታዊ ሸቀጦች ሳይሆኑ የነጋዴዎች መሆናቸውን ከክፍለ ከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ይሁን እንጂ የሕብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጁ ማህበሩ ምርቶችን የሚረከበው ከዩኒየኖች እንጂ ከግለሰብ ነጋዴዎች አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም