የባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ እንቅስቃሴን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ

62
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አሰራርን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያግዝና በኮምፒውተር የታገዘ አዲስ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ስራ ላይ ዋለ። የእቃዎች መጥፋት፣ መንገድ ላይ መዘግየትና ፈጣን የሆነ መረጃ አለማግኘት ችግሮች በአሁኑ ወቅት ከገቢ እና ወጪ እቃዎች የባህር ትራንስፖርት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ናቸው። ዛሬ ይፋ የሆነውና "ካርጎ ካናል" የተሰኘው ቴክኖሎጂ ግን የገቢና ወጪ እቃዎች የባህር ላይ ጉዞና የወደብ ቆይታ ጊዜን ጨምሮ ተያያዥ መረጃዎችን በመያዝ የእቃዎቹን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስለጣን አስታውቋል። አስመጭዎችም ሆኑ ላኪዎች  የወጪም ሆነ የገቢ እቃዎቻቸውን እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎችን ካሉበት ቦታ ሆነው በሞባይል ስልክና ኮምፒዩተር አማካኝነት በቀላሉና በፍጥነት ለመለዋወጥ የሚያስችል አሰራርን ይፈጥራል ተብሏል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር  አቶ መኮንን አበራ እንዳሉት ቴክኖሊጂው በአሁኑ ወቅት በባህርና ትራንስፖርት ሎጅስቲክስ ዘርፍ ላይ የሚታየውን ባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ በመቀየር ከፍተኛ የሆነ ጊዜና ጉልበት መባከንን ያስቀራል። ቴክኖሎጂው በየመንገዱ የሚጠፉ እቃዎችን በመቆጣጠር ከአስመጭዎችና ከላኪዎች ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችንም የሚያስቀር መሆኑን  ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። የሎጅስቲክስ ዘርፉን የበለጠ ለማዘመን የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፤ ዛሬ የተመረቀው ቴክኖሊጂም የእነዚህ ተግባራት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት መረጃዎችን ለመያዝ ይሰራበት የነበረውን የወረቀት አሰራር ወደ ዌብሳይት በመቀየር የተቀላጠፈ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲኖር ያግዛልም ብለዋል። የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂው የተሰራው ኤኤ አድቫንስድ ኢንርሜሽን ቴክኖሎጂ በተሰኘ ኩባንያ እና በኢትዮጵያ ማሪታይማ ባለስልጣን ትብብር ነው። መተግበሪያው ላለፉት ስድስት ወራት ሙከራ ሲደረግበት ቆይቶ አዋጭ ሆኖ በመገኘቱ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ተመርቆ  አገልግሎት ላይ ውሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም