የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ለተሻለ ውጤት እንዳነሳሳቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ

104
ደሴ/ደብረ ብርሃን ጥቅምት 15/2011 በዩኒቨርሲቲውና በደሴ ከተማ ወጣቶች የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ለበለጠ ኃላፊነትና ለተሻለ ውጤት የሚያነሳሳን ነው ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ። የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች አስታወቁ። ከኦሮሚያ ክልል ቡሬ ሆራ አካባቢ የመጣውና በኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ኢተቻ አበበ በወሎ ዩኒቨርሲቲው አመራር፣ በተማሪዎች ኅብረትና በደሴ ከተማ በሚገኙ ወጣቶች ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናውን ገልጿል፡፡ "ከአውቶቡስ ተራ ጀምሮ በመቀበል፣ እቃቸውና በመሸከም፣ ንብረታቸው እንዳይጠፋ በመጠበቅና እስከ ደሴ ካምፓስ ድረስ ትራንስፖርት በማዘጋጀት ኢትዮጵያዊ አንድነት የተገለጸበት አቀባበል ተደርጎልናል" ብሏል፡፡ አቀባበሉ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማን ከማድረጉ ባለፈ የአንድነት መንፈስ የተንጸባረቀበት በመሆኑ ለበለጠ ኃላፊነት ተግቶ ለመስራትና የህዝብን ውለታ ለመክፈል የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግሯል፡፡ "በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው አለመረጋጋት በወላጆች ዘንድ መጠነኛ ስጋት ቢፈጥርም በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አካባቢው የሰላም አምባሳደር መሆኑን ያሳያል" ያለው ደግሞ ከባህር ዳር የመጣውና የ4ኛ ዓመት የጤና ሳይንስ ተማሪ የሆነው አብርሃም ንጋቱ ነው፡፡ የተደረገላቸው አቀባበል አላስፈላጊ ወጭን የቀነሰና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጎለብት በመሆኑ መደሰቱን ተናግሯል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ሕብረት አባል የሆነው ተማሪ ተስፋሁን አሊ በበኩሉ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ፣ የተማሪዎች ኅብረት፣ የደሴና ኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶችና የጸጥታ ኃይሉ በተማሪዎች አቀባበሉ ላይ መሰማራታቸውን ጠቁሟል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ታደሰ በበኩላቸው ዘንድሮ በመደበኛው መርሃ ግብር ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መቀበላቸውንና ከ5ሺህ የሚልቁ አዲስ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ከቅድመ ዝግጀት ሥራዎች መካከል ዩኒቨርሲቲው በ54 ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የማብሰያ ቤቶች ግንባታ ሥራ በኮምቦልቻና ደሴ ካምፓሶች ማከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአንድ ጊዜ እስከ 3ሺህ 500 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ የመመገቢያ፣ የመሰብስቢያና የመዝናኛ አዳራሽ እንዲሁም ክሊኒክ ተገንብቶ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ የተማሪዎች ማረፊያ ክፍሎችንም በጸረ - ተባይ መድኃኒት የመርጨት፣ የማጽዳትና ቀለም የመቀባት ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ዶክተር ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የመማር ማስተማር ስራው ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ በደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገልጸዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ወደዩኒቨርሲቲው ሲመጡ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ባይተዋርነት እንዳይሰማቸው ማድረግን ተናግረዋል ከተማሪዎቹ መካከል ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ተማሪ አዱኛ ነገሬ እንዳለው ከአዲስ አበባ ላምበረት መናኽሪያ ጀምሮ እስከ ደብረ ብርሃን መናኽሪያ ድረስ በተደረገላቸው ልዩ አቀባበል መደሰቱን ተናግሯል፡፡ "ህብረተሰቡ እንደራሱ ልጅ  አቅፎና ተንከባክቦ ሳንገላታና ለዘራፊ ሳንጋለጥ  በፍቅርንና በአንድነትን ያደረገልን መልካም አቀባበል ለአካባቢው ባይተዋርነት እንዳይሰማን አደርጓል" ብሏል፡፡ ከአካባቢው ህብረተሰብና ከወጣቶች ያየውን ሰላምና መረዳዳት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው አጠናክሮ ለማስቀጠል ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ ከጎጃም የመጣችው በዩኒቨርሰቲው የአግሪካልቸር ተማሪ የሆነችው ትጓደድ ጌጤ በበኩሏ ማህበረሰቡ ያደረገላቸው መልካም አቀባበል ለአካባቢው እንግድነት አንዳይሰማት ያደረጋት መሆኑን ተናግራለች፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ እንግዳ ተቀባይና ሰላም ወዳድ መሆኑን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጻ፣  ትምህርቷን ጠንክራ በመማር ቤተሰቦቿና አገሯ የጣሉባትን አደራ ለመወጣት ተግታ እንደምትሰራ ተናግራለች፡፡ የማማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማና ሰላማዊ እንዲሆን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር በአንድነትና በመቻቻል በመኖር የድርሻዋን እንደምትወጣም ቃል ገብታለች፡፡ ልጃቸዉን ደብረብርሃን ዩንቨርሲቲ ለማድረስ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በዩንቨርሲቲው አውቶቡስ አቀባበል እንደተደረገላቸው የገለጹት አቶ ለገሰ ለማ በበኩላቸው "ልጄ ከዚህ ሰላም ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ማህበረሰብ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በመመደቧ በእጅጉ ተደስቺያለሁ" ብለዋል። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ መለሰ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው እንደገለጹት ኮሚቴ በማዋቀር ተማሪዎችን እስከአዲስ አበባ ድረስ በመሄድ እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ 3 ሺህ 607 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል የተማሪዎች ማደሪያ፣ ቤተ መጻህፍት ቤተ ሙከራ፣ መማሪያ ክፍልና የመምህራን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በ2011 በጀት ዓመት በመደበኛ፣ በማታና በርቀት የትምህርት መርሃ ግብሮች 32 ሺህ 455 ተማሪዎችን ተቀበሎ እንደሚያሰለጥን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም