አገራዊ የለውጥ እርምጃዎች ነገ ላቀድነው ራእይ ትልቅ ስንቅ ናቸው-የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ

61
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 መንግስት የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላማዊ ግንኙነትን ከመፍጠር ጀምሮ የወሰዳቸው አገራዊ የለውጥ እርምጃዎች ነገ ላቀድነው አገራዊ ራእይ ትልቅ ስንቅ ናቸው" ሲሉ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ ዛሬ ባካሄዱበት ወቅት የፕሬዚዳንቱን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሏል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርት አመታት የዘለቀውን ጦርነት አፍርሰው የሁለቱ አገር ህዝቦች ዳግም በፍቅር በአንድነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠር ችለዋል። ''ከስድስት ወራት በፊት መንግስት 'ይህንን አደርጋለሁ' ብሎ ቃል ቢገባም እንደ ተስፋ ዳቦ የተለመደ የፖለቲከኞች ቅስቀሳ ተብሎ ነበር የሚወሰደው'' ያሉት ዶክተር ሙላቱ መንግስት ባለፉት ወራት የሚደነቅ ውጤት ሊያስመዘግብ መቻሉን ተናግረዋል። እነዚህ ስኬቶች ነገ ላቀድነው ለአገራዊ  ለውጥ ራእይ ትልቅ ስንቅ መሆኑን ገልጸው የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል መትጋት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። አሁን በተመዘገበው ውጤት መዘናጋት ሳይፈጠር ረዥሙን አገራዊ ራዕይ ከፍጻሜ ለማድረስ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል። ''በመሆኑም በከባድ ዋጋ የተገኙ ስኬቶቻችንን ሳናሳካ እና ከግብ ሳናደርስ ለአፍታም ቢሆን ልናርፍ አይገባንም'' ሲሉ አሳስበዋል። ስኬቶችን ለዘለቄታው ለማስጠበቅ ህዝቡ ከትናንት በተሻለ መልኩ ዛሬ ላይ ለለውጡ ዘብ እንደሚቆም እምነታቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ለብዙ ዘመናት በገናና ስሟና በታላቅነቷ የምትታወቀውን ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት የድህነት አዘቅት ውስጥ ለማውጣትም ሁሉም መረባረብ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት። ፍላጎታችን በበሽታና በእርዛት የሚሰቃየውን ህዝብ መታደግ ላይም በትኩረት በመስራት ሁሉም ሃላፊነት እንዳለበትም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም