ትልቅ አገር ለመገንባት ሠላም ወሳኝ ነው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

85
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011"ትልቅ አገር ለመገንባት ከሠላም ውጪ አማራጭም አቋራጭም የለም" አሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዛሬ ባካሄዱት አስቸኳይ የጋራ ስብሰባ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በሙሉ ድምጽ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። አዲሷ ፕሬዝዳንት በበዓለ-ሲመታቸው ላይ እንደተናገሩት፤ "ትልቅ አገር ለመገንባት ከሠላም ውጪ ምንም አማራጭ አልያም አቋራጭ የለም" ብለዋል። ኢትዮጵያ የኋላቀር አገር ምልክት ሆኖ የቆየችው በዋንኛነት በሠላም እጦት እንደሆነና በተጀመረው ለውጥም ለሠላም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ማስወገድ ይገባዋል ነው ያሉት። ስለዚህም "ሠላም  ከራሳችን፣ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤቶቻችን፣ በመንደራችን፣ በወረዳዎች መካከል፣ በክልሎች መካከል፣ ከጎረቤት አገራት ጋርና  በዲያስፖራም ሊኖር ይገባል" ብለዋል። መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ የጋራ ቤት እንደሚገነቡ በማሰብ እርስ በእርስ በመደማመጥ፤ በመፈቃቀርና በመተሳሰብ ሥራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በተጓዳኝም በሕዝቦች መካከል የሚለያዩትን ነገሮች በማስፋት ወደ ጠብ-አጫሪነት ከመሄድ ይልቅ አንድነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አሳስበዋል። በመሆኑም ለውጡ በተጀመረው መንገድ አንድነትን እያጠናከረ እንዲሄድ ስር የሰደደውን ጥላቻ፣ መናናቅ እና አልፎ አልፎ የሚታየውን ጠብ መግታት ይገባል ብለዋል። ልዩነቶችን ለመፍታት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በዳበረ የቤተ-እምነቶች ጥበብና የሽምግልና ሥርዓት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል። በዚህም ለአሁኑ ትውልድም ሆነ ለቀጣዩ የምታኮራ አገር መፍጠር እንደሚቻል ጠቅሰዋል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ነው ዛሬ የተመረጡት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም