ከማእከሉ የተለቀቀ የማሽላ ዝርያ ተጠቅመን ምርታችንን አሳድገናል- የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች

134
ደሴ ጥቅምት 15/2011 ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማእከል የተለቀቁ የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎችን ተጠቅመን ምርታችንን አሳድገናል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ። በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ አቧሬ 07 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደሳለው አገዘ ለኢዜአ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም የአካባቢ ዝርያ ተጠቅመው በሩብ ሄክታር ማሳ ላይ ከሚዘሩት ማሽላ ከ5 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ ነበር። ከሶስት አመት ወዲህ ከማእከሉ ያገኙትን“ጊራና አንድ” የተሰኘ የማሽላ ዝርያ መጠቀም በመጀመራቸው ከተመሳሳይ ማሳ ላይ 15 ኩንታል ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይ እያገኙት ባለው ምርት የቤተሰባቸውን ቀለብ ለመሸፈን ያስቻላቸው መሆኑን ገልፀዋል። የማሽላ ዝርያው የዝናብ እጥረትን በመቋቋም በሶስት ወር ውስጥ ለምርት የሚደርሰና አገዳው ለቤት መስሪያ፣ ለእንስሳት መኖና ለማገዶ ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል ። ከዚህ ቀደም የአካባቢ ዝርያ ተጠቅሜ አንድ ሄክታር ከሚጠጋ ማሳ ላይ 12 በኩንታል ምርት አገኝ ነበር” ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር በላይ ካሳዬ ናቸው። ከማእከሉ የተለቀቀውን የተሻሻለ የማሽላ ዝርያ መዝራት ከጀመሩ ወዲህ ከተመሳሳይ ማሳ 37 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል ። በሰሜን ወሎ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ እንድሪስ ፈንታው ከምርምር ማእከሉ የተለቀቀ “ጊራና አንድ” የተሰኘ  የማሽላ ዝርያ በመጠቀም  በሄክታር እስከ 74 ኩንታል ምርት ያገኙ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ተናግረዋል ። “የማሽላ ዝርያው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እያገዘ መጥቷል” ብለዋል ። በመኸር ወቅት የማሽላ ዝርያውን በመጠቀም  በዘር ከተሸፈነው 2 ሺህ 431 ሄክታር መሬት ላይ 110 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበው አመላክተዋል ። የምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ጌታቸው ማእከሉ በመኸር ወቅት በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች 992 ኩንታል የተለያዩ የሰብል ዘሮችን ማሰራጨቱን ተናግረዋል ። የሰብል ዝርያዎቹ 4ሺህ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ በሰብል ዝርያዎቹ ከተሸፈነው 1ሺህ 209 ሄክታር ማሳ እስከ 84 ሽህ 630 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም