የሁመራ ሰሊጥ ነጋዴዎች የኢንተርኔት ማዕከል አገልግሎት ባለመጀመሩ ግብይት ለማካሄድ ተቸግረናል አሉ

58
ሁመራ ጥቅምት 15/2011 በትግራይ ክልል ሰቲት ሁመራ ከተማ  በኢንተርኔት/ኦን ላይን/ ግብይት የተገነባው ማዕከል አገልግሎት ባለመጀመሩ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት ለማካሄድ መቸገራቸውን ሰሊጥ  ነጋዴዎች ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በከተማው የማዕከሉን  ግንባታ ካከናወነ  ሦስት ዓመታት አልፎታል። ማዕከሉ በንግዱ ማህበረሰብ ጥያቄ መሠረት ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት  መገንባቱ መልካም ቢሆንም፤ አገልግሎት ባለመጀመሩ ቅር ተሰኝተናል ሲሉ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሰሊጥ ነጋዴዎችንና የአምራቾችን ችግር ለመፍታት የገነባው ማዕከል ሥራ ባለመጀመሩ የአገር ውስጥና የዓለም ግብይት መረጃ ለማግኘት ተቸግረናል ሲሉም ተናግረዋል። ከነጋዴዎቹ አቶ ተመስገን አብራር ማዕከሉ አገልግሎት ባለመጀመሩ የንግዱ ማህበረሰቡ ምርቱን በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ አማራጮችን አፈላልገው ለመሸጥ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ማዕከሉ ሥራ ባለመጀመሩ ነጋዴውም ሆነ የኅብረት ሥራ ማህበራት በውድድር ላይ የተመሰረተ ገበያ ለማግኘት አልቻልንም ያሉት ደግሞ አቶ መስፍን ዘነበ የተባሉ ነጋዴ ናቸው፡፡ አቶ መሐመድ ብርሃን ያሲን የተባሉ ነጋዴ በበኩላቸው ማዕከሉ ወደ አገልግሎት ባለመሸጋገሩ በዞኑ የሚመረተው ሰሊጥ መንግሥትም ሆነ ነጋዴውም በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ አላደረገም ብለዋል፡፡ የማዕከሉ ሥራ አስከያጅ አቶ አታክልቲ አማረ ማዕከሉ ነጋዴዎቹ  ባቀረቡት ጥያቄ  መሠረት ግንባታው መጀመሩንና ያቀረቡትም ቅሬታ ትክክለኛ እንደሆነ ገልጸዋል። ማዕከሉ ዘመናዊና ቀልጣፋ የግብይት አማራጭ እንዲያገኙ ተብሎ ግንባታው እየተካሄደ ቢሆንም፤አገልግሎቱን ለማሟላት የቁሳቁስ ግዢ በመከናወን ላይ  እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ማዕከሉ ከሚያስፈልጉት ስድስት ባለሙያዎች ሁለቱ መቀጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ የትራንስፎርመርና  የኮምፒዩተሮች ግዢ  መከናወኑንና  የኔት ዎርክ ዝርጋታ መጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱ ለማስጀመር የሚያስፈልገው መሣሪያ(ማሽን) ግዢ በዚህ ዓመት እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ ሁመራ በኢትዮጵያ ዋነኛዋ የሰሊጥ አምራች አካባቢ መሆኗ ይታወቃል። ሰሊጥ ከአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ ነው። የኢትዮጵያት ምርት ገበያ ባለፈው ዓመት ካገበያየው ሰሊጥ  ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ አስገኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም