አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆኑ

371
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆኑ። አምባሳደሯ የተመረጡት ዛሬ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት አስቸኳይ የጋራ ስብሰባ ባገኙት የሙሉ ድምጽ ድጋፍ ነው። አምባሳደር ሳህለወርቅ ባለፉት አምስት ዓመታት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን በመተካት ለቀጣይ ስድስት ዓመታት ያገለግላሉ። አምባሳደሯ ላለፉት 30 ዓመታት በብሔራዊ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በውጭ ግንኙነት ሥራ የካበተ ልምድ አሏቸው። አምባሳደር ሳህለወርቅ በ1942 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረ-ማርያም ተከታትለዋል። ከዛም በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከፈረንሳዩ ሞንትፔሊር ዩኒቨርስቲ አጠናቅቀዋል። በፈረንሳይ ከዓመታት ቆይታ በኋላ አገራቸው ተመልሰው በትምህርት ሚኒስቴር በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት ቀጥሎም የሥራ ክፍሉን በኃላፊነት መርተዋል። ይህንንም ተከትሎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ደረጃ ተቀጥረው ሠረተዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች በግጭት አፈታትና በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ሥልጠና ወስደዋል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር ከ1989 እስከ 1993 በሴኔጋል የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር ነበሩ። መቀመጫቸውን ሴኔጋል አድርገውም በተጠቀሱት ዓመታት ለማሊ፣ ለኬፕቬርዴ፣ ለጊኒ ቢሳውና ለጋምቢያ የኢትዮጵያ ተጠሪ አምባሳደር ነበሩ። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1993 እስከ 2002 ደግሞ በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ቋሚ ተጠሪ በመሆን ሠርተዋል። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2002 እስከ 2006 በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅትም ቋሚ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። በድርጅቱ በነበራቸው የተጠሪነት የሥራ ዘመን በተለይም የአክሱም ሃውልት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ልብ ይሏል። በአፍሪካ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ ውስጥም በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት አገልግለዋል አምባሳደር ሳህለወርቅ። መቀመጫቸውን በፈረንሳይ አድርገውም ለቱኒዚያና ለሞሮኮ ተጠሪ አምባሳደር በመሆን ድርብ የሥራ ኃላፊነት ነበረባቸው። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2009 ደግሞ በአፍሪካ ኅብረትና በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሠርተዋል። በመካከልም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር በመሆንም በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል። ይህንን ተከትሎ አምባሳደሯ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የመንግሥታቱ ድርጅት የተቀናጀ የሠላም ጽህፈት ቤት ኃላፊና ልዩ መልዕክተኛም ነበሩ። በኬንያም የመንግሥታቱ ድርጅት ጽህፈት ቤት ጄነራል ዳይሬክተር በመሆን በቀድሞ የድርጅቱ ዋና ጸኃፊ ባንኪሙን ተሹመው ሥራቸውን ሠርተዋል። በወቅቱ አምባሳደሯ ይህንን የድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ከዋና ጸሃፊው ሥር ሆነው ሲቆናጠጡ የመጀመሪያዋ ግለሰብ ነበሩ። ባለፈው ሰኔ ወር የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አምባሳደር ሳህለወርቅን የእርሳቸው የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ አድርገዋቸዋል። በተጓዳኝም በዋና ጸሃፊው ሥር የሚመራውን የድርጅቱ የአፍሪካ ኅብረት ጽህፈት ቤትም የበላይ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ናቸው። በዛሬው ዕለትም አምባሳደሯ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የሥልጣን ዘመናቸውን ከመጠናቀቃቸው አንድ ዓመት አስቀድመው ከኃላፊነታቸው በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ በፕሬዝዳንትነት ተሹመዋል። የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአማርኛ በተጨማሪ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገራሉ። በማኅበራዊ ህይወታቸውም ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 70 ሥር የፕሬዝዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመትና አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዝዳንትነት እንደማይመረጥ ይደነግጋል። ከደርግ ሥርዓተ-መንግሥት ውድቀት በኋላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሽግግር መንግሥቱ ፕሬዝዳንት እንዲሁም ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ መቶ አለቃ ግርማ ወልደ-ጊዮርጊስና ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም