በአሁኑ ሰአት በአገራችንና በህዝቦቻችን ዘንድ የተስፋ ጎህ ቀዷል - ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ

83
አዲስ አበባ 15/2011 በአሁኑ ሰአት በአገራችንና በህዝቦቻችን ዘንድ የተስፋ ጎህ ቀዷል ሲሉ ተሰናባቹ  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። የፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል። የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዘመን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ ዛሬ ባካሄዱበት ወቅት የፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱን የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ተቀብሏል። ፕሬዚዳንት ሙላቱ የስንብት ጥያቄያቸውን ባቀረቡበት ወቅት ለአምስት ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት ኢትዮጵያን የመሩበት ጊዜ በህይወት ጊዜያቸው ውስጥ ከተራመዷቸው እርምጃዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚይዙ እንደሆኑ ገልጸዋል። "የምወደውን አገርና ህዝብ እንደማገልገል ትልቅ እርካታ የሚሰጥ ተግባር የለም" የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይሄን እድል ለሰጣቸው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያና ህዝብና መንግስት ምስጋና አቅርበዋል። አቅማቸውና እውቀታቸው በፈቀደው ሁሉ የተጣለባቸው ሃላፊነት በታማኝነት መፈጸማቸውንና ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል። በርዕሰ ብሔርነት ኢትዮጵያን በመሩበት አምስት ዓመታት ውስጥ ሶስቱ ዓመታት በአመዛኙ አገሪቷ በትልቅ ፈተናና ስጋት ውስጥ ወድቃ እንደነበርና ብሔራዊ ደህንነቷም ላይ ትልቅ አደጋ የተጋረጠበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል። የዜጎች የዴሞክራሲ፣ የልማት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የህግ የበላይነት ጥያቄ ባለመመለሱ ምክንያት በተቀሰቀሰው ቁጣ ምክንያት ኢትዮጵያን እንደ አንድ መቀጠሏን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ጊዜ እንደነበረም ነው ያስረዱት። ከ6 ወራት በፊት የነበረውን ጊዜ ማስታወስ ግድ እንደሚልና ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ውስጥ ገብታ እንደነበር አመልክተዋል። ዛሬ የፀደይ ወራት ላይ ደርሰናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በአገራችንና በህዝቦቻችን ዘንድ የተስፋ ጎህ መቅደዱን ተናግረዋል። ''ዓለምን ያስደነቁት የለውጥ እርምጃዎች ይመጣሉ ብሎ ከቶ ያሰበ እንዳልነበረና ያልተጠበቀ ነበር'' ብለዋል። በነዚህ ጊዜያት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች የተፈቱበት በውጭ አገሮች የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው በመግባት አማራጭ የፖለቲካ ሀሳባቸውን ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እስረኞችን ከመፍታት ጀምሮ በትጥቅ ትግል የነበሩ ድርጅቶች ወደ አገር በመግባት በሰላማዊ ትግል ለመሳተፍ መወሰናቸውንም አንስተዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት የዘለቀ የጦርነትን ግንብ አፍርሰው የሁለቱ አገሮች ህዝቦች ዳግም በአንድነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠር መቻላቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ''በስድስት ወራት ውስጥ የተመዘገቡት ስኬቶች ነገ ለታቀደው አገራዊ ውጥንና ራዕይ ትልቅ ስንቅ እንደሆኑና ያም ቢሆንም ባገኘናቸው ውስን ስኬቶች ተከልለን የረጅም ጊዜ ራዕያችን ልናሰናክል አይገባም'' ብለዋል። አገራዊ እድገት የለማዊና ዴሞክራሲያዊ ግቦቻችን ሳናሳካ ለአፍታም ቢሆን ማረፍ እንደማይገባና ይልቁንም በከባድ ዋጋ የተገኙ ስኬቶቻችንን ከፍ ወዳለ የእድገት ማማ ለመውጣት የበለጠ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ለተገኙት ስኬቶች ህዝቡ ዋነኛ የድሉ ሞተርና ባለቤት እንደሆነና ስኬቱንም ለማስቀጠል ህዝቡ ከትናንት በተሻለ ለለውጡ ዘብ መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ መስራት እንደሚገባውም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም