ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

76
ጥቅምት 14/2011 በኢትዮጵያ እያደገ እና እየተነቃቃ የመጣውን የኢኮኖሚ ዕድገት በመደገፍ፤ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሰማሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ፡፡ በሳውዲ ዓረቢያ አስተናጋጅነት ’’መፃዒ የኢንቨስትመንት ኢንሼቲቭ ፎረም’’ በሪያድ ለሶስት ቀናት ተካሂዷል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በፎረሙ ላይ እንደተናገሩት ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት አፍሪካን እና የዓለም ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ ይችላል፡፡ ዘመኑ አብሮ ተደጋግፎ ለማደግ እና ለማትረፍ የሚያመች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል። ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ተወዳዳሪ የሰው ሃብት፣ የገበያ ተደራሽነት እና የተሻሻሉ ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችሉ አቅሞች መሆናቸውንም ነው አቶ ደመቀ የጠቀሱት፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች ሃገሪቱ ካለችበት የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ አንፃር የማይታለፍ ዕድል ነውም ብለዋል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም እና ቀጠናዊ ቅንጅት ለአፍሪካ አህጉር ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቱንም በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት፣ በደቡብ ሱዳን የተደረሰው የሰላም ስምምነት እና የሱማሊያ መንግስት መጠናከር አፍሪካን ለኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻነት ተስፋ የለገሱ የፖሊሲ ለውጦች መሆናቸውንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት መንግስት ሳቢ እና ምቹ ማበረታቻዎችን ማዘጋጀቱን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገሪቱ ላለፉት ዓመታት ያስቀጠለችው ዘላቂ እና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ለአፍሪካ ኢንቨስትመንት ዋስትና እንደሚሰጥም ነው የገለፁት፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም