በተደረገልን ደማቅ አቀባበል ተደስተናል --- የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ተማሪዎች

121
መቀሌ ጥቅምት 14/2011 በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በተደረገላቸው አቀባበል   መደሰታቸውን ገለጹ፡፡ በ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ከተመደቡ ተማሪዎች አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተደረገላቸው አቀባበል አስደሳችና ከጠበቁት በላይ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ የመጣው ተማሪ ዳዊት አየለ "የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎችና የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ብዙ እርቀት መጥተው ያደረጉልን አቀባበል ከጠበኩት በላይ ነው" ብሏል፡፡ ከእዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ወጥቶ እንደማያውቅና የመቀሌ ከተማ የመጀመሪያው እንደሆነች የተናገረው ተማሪ ዳዊት "ለተወሰነ ጊዜ የቤተሰብ ናፍቆት ቢሰማኝም ሁለተኛ ቤቴ ይሆናል ብዬ አስባለሁ"  ሲል ተናግሯል፡፡ ከአዳማ  ከተማ የመጣውና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኢንጅነሪን ትምህርት ክፍል የተመደበው ተማሪ ኤፍሬም ወልደስላሴ በበኩሉ በመጀመሪያ ምርጫው በመመደቡ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ  በመቀሌ ከተማ ነዋሪና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተደረገለት አስደሳች የሆነ አቀባበል ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ ከሃዋሳ ከተማ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጣችው ሌላዋ ተማሪ ወይንሸት መላኩ በበኩሏ " በዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመመደቤ ደስተኛ ነኝ " ብላለች፡፡ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎችን ጨምሮ ከከተማዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተወጣጡ አካላት በተደረገላት ደማቅና አስደሳች አቀባበል መደሰቷን ገልጻ፣ በእዚህም እንግልት ሳይደርስባት ወደ ዩኒቨርሲቲው  መግባቷን ተናግራለች፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ  ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብደልቃድር ከድር  በበኩላቸው ተቋሙ በዘንድሮው ዓመት አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችን ለመቀበል ካለፈው ክረምት ጀምሮ በቂ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ለመማር ማስተማሩ ስራ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች መሟላታቸውን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማደራጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ዶክተር አብደልቃድር ገለጻ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ እንዲኖር ከመቀሌ ከተማ አስተዳድር፣ ከከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዲን ዶክተር ከሳቴ ለገሰ በበኩላቸው እንዳሉት ለተማሪዎች አገልግሎት የሚውሉ  የመመገቢያ፣ የመኝታ፣ የመዝናኛና የህክምና መስጫ ክፍሎች አስፈላጊው ጥገናና እድሳት ተደርጎላቸው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን  ከአየር ማረፊና ከአውቶብስ መናኸሪያ በመቀበል ወደ ዩኒቨርሲቲ  የሚያደርሱ አውቶቡሶች ቀድመው እንዲመደቡ በመደረጉ ተማሪዎች ሳይንገላቱና መጉላላት ሳይደርስባቸው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ገብረሐዋሪያ ተአምራት አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል 157 በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች መሰማራታቸውን ተናግሯል፡፡ ተማሪዎች በምዝገባ ወቅት እንዳይቸገሩ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከተማሪዎች ህብረት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ተወካይ የሆኑት አቶ በየነ ይልማ በበኩላቸው "ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባይታወርነት ሳይሰማቸው ትምህርታቸውን ተረጋግተው በሰላም እንዲማሩ ከዩንቨርሲቲው ጋር ተቀራርበን በጋራ እንሰራለን" ብለዋል፡፡ ከመቀሌ ከተማ በ10 ኪሎ ሜተር እርቀት ላይ የምትገኘው ኩሓ ከተማ ድረስ በመሄድ ለተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችህ አቀባበል ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው የትምህርት ዘመን 5 ሺህ 890 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ጨምሮ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች 30 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም