በምዕራብ ጎንደር የደረሰ የሰሊጥ ሰብል በዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ ነው

55
መተማ ጥቅምት 14/2011 በምእራብ ጎንደር ዞን የደረሰ የሰሊጥ ሰብል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እየተሰበሰበ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ ከተያዘው ወር መጀመሪያ ጀምሮ ከ163 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ሰብሉ መሰብሰቡን መምሪያው ገልጻል። በመምሪያው የሰብል ልማት ጥብቃ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በ191 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከለማው የሰሊጥ ሰብል ውስጥ 163 ሺህ ሄክታሩ በዝናብ ጉዳት ሳይደርስበት ተሰብስባል። "እስከ ህዳር አጋማሽ ባላው ጊዜ ውስጥ ቀሪው ሰብል ከማሳ ላይ ይሰበሰባል" ብለዋል። በሰብል ስብሰባው ወቅት በምርት ላይ የጥራት ጉድለት እንዳያጋጥም ለአርሶ አደሩ በሚደረጉ ጥንቃቄዎች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው መደረጉን  ተናግረዋል። በመተማ ወረዳ የመሸሃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉጌታ አስናቀው እንደተናገሩት ከ10 ሄክታር የደረሰ የሰሊጥ ማሳ ውስጥ ስድስት ሄክታሩን ሰብስበዋል። "በዝናብ መብዛ የጠበኩትን ያክል ምርት አገኛለሁ የሚል እምነት ባይኖረኝም የምርቱን ጥራት ለመጠበቅ በወቅቱ እየወቃሁ ነኝ" ብለዋል። "ከአራት ሄክታር ማሳየ ላይ የደረሰ የሰሊጥ ሰብል ሙሉ ለሙሉ ሰብስቤያለሁ " ያሉት ደግሞ በወረዳው የለምለም ተራራ ቀበሌ  ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃኑ መኮንን ናቸው። አርሶ አደሩ ከሰበሰቡት የሰሊጥ ሰብል ውስጥ ገሚሱን በመውቃት 42 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በወረዳው የደለሎ እርሻ ልማት ባለሃብት አቶ ጀጃው አብርሃ በበኩላቸው 30 ሄክታር መሬት ላይ ከደረሰ የሰሊጥ ሰብል ውስጥ ገሚሱን መሰብሰባቸውን ገልፀዋል። በዞኑ ታርሶ በሰሊጥ ዘር ከተሸፈነው መሬት ይገኛል ተብሎ የተጠበቀው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በበክረምት ወቅት በነበረው የዝናብ መጠንና ስርጭት መብዛት ቅናሽ እንደሚኖረው በምርት ግምገማ መታወቁን የመምሪያው መረጃ አመላክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም