ኢትዮጵያ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ጋር ያላትን ትብብርና ወዳጅነት ማጠናከር ትፈልጋለች

103
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 ኢትዮጵያ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ጋር ያላትን ትብብርና ወዳጅነት ማጠናከር እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። ሚኒስትሩ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ዳይሬክተር ጀኔራል ጆሴ ግራዚያኖ ሲልቫ ጋር በጣሊያን ሮም ተነጋግረዋል። ዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላት ትብብርና ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ፍላጎቷ መሆኑን ለድርጅቱ ዳይሬክተር ጄኔራል እንደገለጹላቸው የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ጆሴ ሲልቫ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች እየተካሄደ ላለው ለውጥ ተቋማቸው አድናቆት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው የጣልያን-አፍሪካ ትብብር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመታደም ወደ ጣሊያን ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከመድረኩ በተጓዳኝ ከጣልያን ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽና ቀጠናዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም