ኢትዮጵያና አዘርባጃን በወጣቶችና ስፖርት መስክ በትብበር መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያዩ

59
አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 ኢትዮጵያና አዘርባጃን በወጣቶችና ስፖርት መስክ በጋራ መስራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ  ምክክር አድርገዋል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ኤልማን አብዱላዬቭ ጋር ተወያይተዋል። አቶ ርስቱ ኢትዮጵያ በወጣቶችም ሆነ በስፖርት ጉዳይ ከአዘርባጃን ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጐት እንዳላት ገልጸዋል፡፡ አዘርባጃን በቼስና በቴኳንዶ ስፖርት የካበተ ልምድ ያላት አገር መሆኗን በመግለጽ የተለያዩ አህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮችንም በማስተናገድ አዘርባጃን ልምድ ያላት መሆኗን አምባሳደሩ አንስተዋል። በአትሌቲክስ ስፖርትና በወጣቶች መድረክ ዙሪያ አዘርባጃን ከኢትዮጵያ ልምድ መወሰድ እንደምትፈልግ ተናግረዋል። የሁለቱ አገሮች የስፖርትና የወጣቶች ፌዴሬሽኖች ተቀራርበው እንዲሰሩ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ መዘጋጀት እንዳለበት መስማማታቸውን ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና አዘርባጃን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1992 ነው። አዘርባጃን በሚያዚያ ወር 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን የከፈተች ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም በአዘርባጃን ርዕሰ መዲና ባኩ የቆንጽላ ፅህፈት ቤት ከፍታለች። የአዘርባጃን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤልማር ማማድያሮቭ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መወያያታቸው ይታወሳል። በወቅቱ የአዘርባጃን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቆይታቸው አገሮቹ በፖለቲካው መስክ ያላቸውን ትብብር ለማጠከር የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ከኢትዮጵያ አቻቸው ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተፈራርመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም