የፋይናንስ ሥርዓቱ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዳይጎለብት አድርጓል - ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

108
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 የአገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት የፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዳይጎለብት ዋነኛ ማነቆ ነው ተባለ። ይህን ያለው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ለዲጂታል ኢኮኖሚው እውቅናና ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል ብሏል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በርካታ አገሮች በሳይንስ፣ ፈጠራና በቴክኖሎጂ ልህቀት ላይ የደረሱት በፈጠራና ቴክኖሎጂ ለተሰማሩ ሳይንቲስቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ በመስጠት መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት። ቢሊየነሩን የማይክሮ ሶፍት ባለቤት ቢልጌት እና የፌስቡክ መስራቹን ማርክ ዙከር በርግ አብነት በመጥቀስ ከስኬት ማማ የወጡ የፈጠራ ባለቤቶች ምስጢር የፈጠራ ንድፋቸውን ወደ ምርት የቀየሩባቸው አስቻይ ሁኔታዎች መኖር ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ "ከዙከር በርግና ቢልጌትስ የተሻሉ ዓለምን ሊቀይሩ የሚችሉ የፈጠራ ንድፈ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች አሉ" ያሉት ዶክተር ጌታሁን ነገር ግን "የፋይናስ ስርዓቱ ከፈጠራ ሃሳባዊያንና ዕውቀት ጋር የተስማማ አይደለም" ብለዋል። የባንኮች፣ የመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አበዳሪ ተቋማት የፋይናንስ ስርዓት ለተዳሳሽና ተጨባጭ ቁሳዊ ነገሮች እንጂ ለፈጠራ ንድፈ ሀሳብና ዕውቀት ድጋፍና እውቅና የሚሰጥ አለመሆኑንም ጠቁመዋል። በትምህርት ላይ የሚገኘው አዲሱ ትውልድ ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ባሻገር ከማይታይ ዓለም ጋር ተግባቦት የፈጠረበት ዲጂታል ዜግነት ባለቤት እንደሆነም ይገልጻሉ። በአገሪቷ ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በትምህርት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትሩ የፋይናንስ ስርዓቱ ለቁሳዊ ነገሮች ብቻ ትኩረት መስጠቱ ጊዜ ያፈበት አሰራር እንደሆነም አንስተዋል። አገሪቷን ለመለወጥ ለዲጂታል ኢኮኖሚው ዕውቅናና ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግም አክለዋል። በተለይም በፈጠራና ቴክኖሎጂ መስክ መስራት የሚሹ ወጣቶችን የትምህርትና የስራ አካባቢያቸውን ምቹ ያደርጋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው የፋይናስና የትምህርትን ስርዓቱ ዲጂታል ኢኮኖሚን ታሳቢ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም