ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ግንኙነቷን ለማጠናከር እንደሚትሰራ ገለጸች

69
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ የአገሪቱ ብሄራዊ አስመጪና ላኪ ኩባንያ አስታወቀ። በኳታር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር መታሰቢያ ታደሰ ከኳታር ብሄራዊ አስመጪና ላኪ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃሰን አል ኪያሚ ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። አምባሳደር መታሰቢያ ኩባንያው በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚችሉባቸውን አመቺ ሁኔታዎች በመጠቀም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል። ኩባንያዎቹ በተለይም የኢትዮጵያን ምርቶች ለኳታር ገበያ እንዲያቀርቡ ጥሪ ማቅረባቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መረጃ አመላክቷል። የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃሰን አል ኪያሚ በበኩላቸው ኩባንያው የምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በማስመጣትና በማከፋፈል የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያን ስጋ፣ ቡናና ጥራጥሬ ምርቶች ለኳታር ገበያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ኩባንያው ያሉትን አመቺ ሁኔታዎችና ለኳታር ገበያ ተስማሚ የሆኑ የገበያ አማራጮችን ለማየትም በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርግ ዋና ስራ አስፈጻሚው መግለፃቸውን ጽሕፈት ቤቱ ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም