ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ሳተላይት ወደ ህዋ ልታመጥቅ ነው

123
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ጥቅምት ወር አጋማሽ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ የሚያስችለውን ዓለም አቀፋዊ ፈቃድ ማግኘቱንም ገልጿል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም በተካሄደው 1ኛው የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክር ቤት ጉባኤ ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ መገለጹ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "ሳተላይት የማምጠቁ ሂደት የት ደረሰ? " ሲል የኢንስቲትዩቱን ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይን አነጋግሯል። ዶክተር ሰለሞን በሰጡት ምላሽ፤ የኢትዮጵያና ቻይና መሐንዲሶች በጋራ በመሆን ወደ ህዋ የምትመጥቀውን ሳተላይት የመገንባቱን ተግባር እያገባደዱ ናቸው። ሳተላይት ማምጠቅ የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ ፈቃድና የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ምዝገባ መጠናቀቁን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር  ጥቅምት 15 ቀን 2019 ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ህዋ እንደምታመጥቅ ተናግረዋል። ሳተላይቷን ከቻይና በማምጠቅ በአራት ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ዶክተር ሰለሞን አብራርተዋል። ሰባ ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ሳተላይቷ ዋና አገልግሎቷ ለግብርና፣ ለውኃ ፣ለማዕድን፣ ለከተማ ልማት እንዲሁም ለአየር ንብረት ቁጥጥርና ክትትል የሚሆኑ መረጃዎችን ማቀበል እንደሆነም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ሳተላይቷ በሃምሳ አራት ቀናት ዓለምን፤ በአራት ቀናት ደግሞ ኢትዮጵያን በመዞር ተልዕኮዋን እንደምታከናውንም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2009 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ2017 ዓ.ም ከስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ተጠቃሚነቷ የጎለበተ ኢትዮጵያን የመፍጠር ራዕይም ሰንቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም