ህጻናትን በመስሪያ ቤቶች ማቆያ ለሚያውሉ እናቶች የትራንፖርት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቀቀ

91
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 በመንግስት መስሪያ ቤቶች በተቋቋሙ የህጻናት ማቆያ ልጆቻቸውን የሚያውሉ እናቶች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ። የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር በስራ መግቢያና መውጫ ሰአት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ተመቻችቶላቸዋል። የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ሴት የመንግስት ሰራተኞች ልጆቻቸውን በተቋማቸው ባለ የህጻናት ማቆያ እንደሚገለገሉ የሚገልጽ ደብዳቤ ከመስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ በማጻፍ ለድርጅቱ መላክ አለበት። በተጨማሪም የህጻኑ/ኗ/ እናት ትክክለኛነቱን የሚያረጋግጥ የልደት ምስክር ወረቀት፣ የህጻኑ እናት ሙሉ ስምና አድራሻ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱን የሚያገኙበት ቦታና ልዩ ስም የሚገልጽ ደብዳቤ ከመስሪያ ቤቱ በቅጽ ተሞልቶ በሸኚ ደብዳቤ ተረጋግጦ መላክ ይኖርበታል። አገልግሎቱን የሚያገኙት ከ3 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ብቻ እንደሆነ በመግለጽ ለህጻናቱና ለእናቶቻቸው በቅድሚያ የሚስተናገዱበት የተዘጋጀላቸው ወንበሮችና ልዩ መታወቂያ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል። መረጃዎችን የሚያደራጁ የሚመለከታቸው አካላትና እናቶች አስፈላጊውን መረጃዎች በላኩበት ወቅት ድርጅቱ  አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን የአገልግሎቱ መግለጫ አመልክቷል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም