የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በይፋ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ

65
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ዛሬ በይፋ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት ወር በፊት ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የትረስት ፈንዱ እንዲቋቋም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው እንደነበረ ይታወሳል። በይፋ የተቋቋመው ትረስት ፈንድ በዛሬው ዕለት ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ በይፋ ሥራ እንዲጀምር ላደረጉት ትጋትና ጥረት አባላቱን በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አመስግነዋል። በአሁኑ ወቅት በትረስት ፈንዱ ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዳለና ከዚህም በኋላ ብዙ ስራ መስራት እንደሚገባ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። የትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤቱ የፈንዱን አቅምና ውጤታማነት ለማሻሻል በትጋት መስራት እንዳለበትም ዶክተር አብይ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የሚሰጡትን የተወሰነ ገንዝብ በአንድ ወይም በሁለት ጊዜ ጠቅልለው በመክፈል በጣም ወሳኝ ለሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንዲያፋጥኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። በቀን ከአንድ ዶላር በላይ መስጠት ለሚችሉ ዜጎች ድጋፋቸውን በፍጥነት እንዲያድርጉና ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ከትረስት ፈንድ ምክር ቤቱ ጋር ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ዶክተር አብይ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ የተመረጡ ሲሆን ስም ዝርዝራቸው በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም መጠቆማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የላከው መግለጫ ያስረዳል። ፈንዱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማቀናጀትና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የባንክ ሂሳብ ቁጥሩም 1000255726725 ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል። በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀን ቢያንስ 1 የአሜሪካ ዶላር በመለገስ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም