አላማጣ ወደ ቀደመ ሰላሟ ተመልሳለች

59
ማይጨው ጥቅምት 13/2011  በአላማጣ ከተማ ትናንት ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ከቀትር በኋላ ተጀምሯል፡፡ በከተማው የሚኖሩ 30 የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎች ከከተማው ኮማንድ ፖስት ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሃገር ሽማግሌዎች በደረሰው ጥፋት ማዘናቸውን ገልጸው አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እራሳቸው እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል። የከተማው ከንቲባና የኮማንድ ፖስቱ አባል አቶ ሃብታሙ ወረታ ትላንት ከአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለጹት አካባቢውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረት አሁን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሷል። እንደዚሁም በግጭቱ በመሳተፍ ለሰው ህይወትና ንብረት ጉዳት ተጠያቂ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ወጣቶች የማጣራት ተግባር እስኪጠናቀቅ በምርመራ ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል። በምርመራ ሒደቱም ነጻ ሆነው የተገኙ አካላት የሚለቀቁ ሲሆን በወንጀሉ እጃቸው ያለባቸው አካላት ግን ለፍርድ የሚቀርቡ መሆናቸውንም ከንቲባው ተናግረዋል። ግጭቱን ለማብረድ በአካባቢው የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብቶ ባከናወነው ስራ ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አገልግሎት መጀመሩን አስረድተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም