"በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርጌ እሰራለሁ" - የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

70
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቀሪ ዘመናቸው በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት አንደሚፈልጉ ተናገሩ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መጎልበት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናና ሽልማት አበርክቶላቸዋል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዲጂታል ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትሪሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሃብት ያንቀሳቅሳል። "ዓለማችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ያለ ዲጂታል ኢኮኖሚ ፈጣን እድገት ማሰብ አይቻልም" ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር  በቀሪ ዘመናቸው ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ አተኩረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ የፈጠሯቸውን ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች በማጠናከር ለዕቅዳቸው መሳካት እንደሚጠቀሙባቸውም ተናግረዋል። የዘመኑ ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ተደራሽነት አንጻር ዕድለኞች በመሆናቸው መልካም አጋጣሚውን በመጠቀም ለፈጠራ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጡም አስገንዝበዋል። በሌላ በኩል ወጣቶች ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በቂ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውም ተናግረዋል። ወጣቶች በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ እንዲሳተፉ መንግስትና ባለሃብቶች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ምክረ ሃሳብ ሰንዝረዋል። በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲጎለበት የሚያስችሉ ኢንስቲትዩቶች የተቋቋሙት በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን መሆኑ ይታወቃል። በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኑርልኝ ተፈራን ጨምሮ በዘርፉ የሚሰሩ ኢንስቲትዩቶች ዳይሬክተሮች አቶ ኃይለማርያም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው ስላበረከቱት አስተዋጽኦ መስክረዋል። አቶ ኃይለማርያም በተለይም ኢትዮጵያን በህዋ ሳይንስ ምርምር ተሳታፊ ለማድረግ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተደራጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም