በጉጂ ዞን ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ልባሽ ጨርቅ ተያዘ

63
ነጌሌ ጥቅምት 13/2011 ከሞያሌ ተነስቶ ወደ ሃዋሳ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሊገባ የነበረ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ልባሽ ጨርቅ መያዙን የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ  አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጎሳዬ ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት ትናንት ሻኪሶ ከተማ ላይ የተያዘው 180 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ ነው። ልባሽ ጨርቁ የሰሌዳ ቁጥራቸው ኮድ 3-01396 አ.አ እና ኮድ 3 -22542  በሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ በፖሊስ ኃይልና በሕብረተሰቡ ትብብር ሊያዝ ችሏል። " ከእቃው ጋር የተያዙ ሁለቱ አሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመስርቶባቸዋል" ብለዋል። የዕቃው ባለንብረቶችን ለመያዝም የማጣራት ሥራው እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አዛዡ ንብረቱንም ለጉምሩክ አካላት ዛሬ ማስረከባቸውን ጠቁመዋል። ኮማደር ጎሳዬ እንዳሉት ጨለማን ተገን በማድረግ ከሞያሌ ወደ ሃዋሳ ሲጓጓዝ የተያዘው ልባሽ ጨርቅ ከ300 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ነው። በሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የነገሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ቡልቲ ልባሽ ጨርቁን በተረከቡበት ወቅት እዳሉት ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው። ባለፉት ሦስት ወራት በተካሄደው እንቅስቃሴም ከሞያሌና ዶሎ አዶ ወደመሀል ሀገር ሊገቡ የነበረና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በጸረ ኮንትሮባንድ ግብረኃይሉ ትብብር መያዛቸውን አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም