ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል

74
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ በኒውዮርክ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ተነገረ። በድርጅቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ የቡድን 77፣ በማደግ ላይ ያሉ አገራትንና የአፍሪካን ቡድን በመወከል ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ 2ኛው ኮሚቴ ንግግር አድርገዋል። ባለፈት 25 ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን የሚልቅ ህዝብ ከድህነት የወጣ ቢሆንም በማደግ ላይ ባሉ አገራት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ። ችግሩ በተለይም በአፍሪካ የባሰ መሆኑን አምባሳደር ገበየሁ አውስተዋል። ዘለቄታዊ የልማት ግብ መስፈርቶችን በማሟላት የድህነት ቅነሳን ዕውን ማድረግ ፈተና መሆኑን በመጠቆም አጀንዳ 2030ን ለማሳካት ጸረ-ድህነት እንቅስቃሴውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማፋጠን ይገባል። የድህነት ቅነሳ እንቅስቃሴው አበረታች ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመልካም አስተዳደር ችግርና በተቋማት የአቅም ማነስ ሳቢያ የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብ አለመቻሉ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ተርታ ለመውጣት ተግዳሮቶች ናቸው። ኢትዮጵያ የጸረ-ድህነት ትግሉን በማጠናከር ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን የጠቆሙት አምባሳደሩ በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት የተቀናጀ የግብርናና የኢንዱስትሪ ልማት ፓሊሲዎችን በመተግበር እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገቧን ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆኑ እንዲሁም ሰፊ የሰው ኃይል የሚጠቀሙ ቀላል የማምረቻ ዘርፎችን የማስፋፋት ስራ እያካሄደች መሆኑን ጠቅሰዋል። በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመረቀውን የአዳማ የኢንዱስትሪ መንደርም ለአብነት አንስተዋል። ኢትዮጵያ የተመድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ)ን ፕሮግራም በመተግበር ላይ መሆኗንና የኢንዱስትሪ ልማት ተግባሯ እንዲጎለብት ለተባበሩ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን አጋሮች ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም