በመቀሌ ነጻ የማህፀን በር ካንሰር ምርመራና ፅንስ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

69
መቀሌ ጥቅምት 13/2011 የመቀሌ ዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የአሜሪካ የማህፀን ህክምና ባለሙያዎች በትብብር ነጻ የማህፀን በር ካንሰር ምርመራና ፅንስ የህክምና አገልግሎት ከትናንት ጀምሮ በመስጠት ላይ ናቸው። በሆስፒታሉ የማህፀን ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ሓጎስ አብርሃ ዛሬ እንዳሉት ለአንድ ሳምንት በሚሰጠው አገልግሎት ከትግራይ ክልልና ከአዋሳኝ ክልል ወረዳዎች ወደ ሆስፒታሉ ለሚመጡና የማህፀን ችግር ያለባቸው ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ። የበር ማህፀን ካንሰር በሽታ የሚከሰተው በአባለ ዘር በሽታ፣ያለ ዕድሜ ጋብቻ በመፈጸም፣በአስገድዶ መደፈር፣ በልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነትና በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። በሽታው በአብዛኛው ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 የሆኑ ሴቶችን እንደሚያጠቃ የተናገሩት ዶክተር ሓጎስ፣ ህመሙ ተገቢው ህክምና ከተደረገለት በቀላሉ እንደሚድን አስረድተዋል። ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ካልተደረገለት ግን እስከ ሞት እንደሚያደርስም ገልጸዋል። በአሜሪካ የኩዩር ሰርቪካል ካንሰር ድርጅት መሥራችና ዳይሬክተር ዶክተር ፓትረሺያ ጎርደን በበኩላቸው በየዕለቱ ለ50 ሴቶች ምርመራ በማድረግ በቆይታቸው ለ300 ሴቶች አገልግሎቱን ለመስጠት መታቀዱን አስታውቀዋል። ከህክምናው በተጨማሪ ባለሙያዎችን እንደሚያሰለጥኑም ተናግረዋል። በዓይደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አዋላጅ ነርስ ሳራ ባህታ የማህፀን በር ምርመራ ለሴቶች አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ካንሰር ሳይቀየር መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል። በሽታው በጊዜው ካልታከሙት ለዕድሜ ልክ ስቃይ በመዳረጉ አስቀድሞ ለመከላከል ትኩረት በመስጠት ምርመራ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በነጻ የህክምና ምርመራው ተጠቃሚ ከሆኑ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሶፊያ ኑሩ እንዳሉት፣የማህፀን ህክምና በማድረግ በሽታው መከላከል ችለዋል።ቤተሰቦቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ሕክምናውን እንዲያገኙ ትምህርት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። ወይዘሮ ህይወት ብርሃነ የተባሉ ተገልጋይ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ህክምና ተደርጎላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ዘንድሮ በተሰጠው ነጻ የህክምና አገልግሎት ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል። የአሜሪካ የማህፀን ህክምና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት አገልግሎቱን ሲሰጥ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። በዓለም በየዓመቱ የማህፀን በር ካንሰር ህክምና የማያገኙ ከ300ሺህ በላይ ሴቶች ለሞት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም