በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ የቢዝነስ መድረክ ተካሄደ

56
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011  በደቡብ ኮሪያ ሴኦል ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከደቡበ ኮሪያ ግዮንዥ  ግዛት አነስተኛና መካከለኛ ኩባንያዎች ማህበር ጋር በመተባበር የቢዝነስ መድረክ ተካሄደ፡፡ በመድረኩ ላይ በኮንስትራክሽን፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣በውበትና ንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡ የኤምባሲው ተወካይ ቤኩማ መርዳሳ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክትም በኢትዮጵያ ያለው የኢኮኖሚና የፓለቲካ ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች እድሉን እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል፡፡ በኤምባሲው የቢዝነስ ዲፐሎማሲ ሚኒስትር አማካሪ አቶ አምሃ ኃይለጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሁም ማበረታቻዎችን በተመለከተ ለኩባንያዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር ኪም ያንግ ኪ በበኩላቸው የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዕዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ልዩ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው በቅርቡም የተወሰኑ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ አነስተኛና መካከከለኛ ኩባንያዎችን ውጤታማነት ለመደገፍ የተቋቋመ ሲሆን ከ250 በላይ ኩባንያዎችን በስሩ ያቀፈ የመጀመሪያው ማህበር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም