ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀኑ

91
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሳዑዲ አረቢያ በሚካሄደው የኢንቨስትመንት መድረክ ለመሳተፍ ወደ ሪያድ ማምረታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳዑዲ አረቢያ በሚኖራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሰልጣናት ጋር በሚያደርጉት ውይይት የኢትዮጵያን አመቺ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ያስተዋውቃሉ። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ትስስር ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል። የኢንቨስትመንት መድረኩ የተለያዩ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች አውቀው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና አለው። በጉባኤው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤልም እንዲሚሳተፉ ተገልጿል። ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፤ የሳዑዲ አረቢያ ባለሀብቶችም በተለያዩ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እንዲሁም የትምህርት መስኮች ተሰማርተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1948 ነው። ሁለቱ አገሮች በንግድ፣ በባህልና ህዝብ ለህዝብ ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሚያደርጉ አገሮች በዋንኛነት የምትጠቀስ አገር ናት። የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደል  አዲል አል ጁቤር በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር በሚያጠናከሩበት ሁኔታ ላይ መወያያታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከአምስት ወር በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እስረኞች እንዲለቀቁ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የሳዑዲ መንግስት ኢትዮጵያውያን እስረኞችን መፍታቱም ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም