በቀጣዮቹ ቀናት የሚኖረው ዝናብ ለእርሻ ስራዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገለጸ

93
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 በቀጣዮቹ 10 ቀናት የሚጥለው ዝናብ ለእርሻ ስራዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚጥለው ዝናብ በአካባቢው ለሚደረገው የማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥሩ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጿል። በተመሳሳይ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የእርጥበት ሁኔታው ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ቀደም ብለው በተዘሩና ፍሬ በመሙላት ላይ የሚገኙ፤ ዘግየተው ለተዘሩና በተለያየ የዕድገት ደረጃ ለሚገኙ የመኸር ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ወሳኝ ሚና ይኖረዋልም ነው ያለው። በተጨማሪም በአካባቢው ለሚገኙ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለግጦሽ ሳር ልምላሜ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኤጀንሲው አስታውቋል። በአንዳንድ ቦታዎች የሚጠበቀው ወቅቱን ያልጠበቀ የእርጥበት ሁኔታ የዕድገት ደረጃቸውን ጨርሰው በመድረቅ ላይ ለሚገኙ ሰብሎች አሉታዊ ጎን ሊኖረው ስለሚችል አስፈላጊውን ቅድመ-ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተመልክቷል። ስለዚህም የዕድገት ደረጃቸውን ጨርሰው በመድረቅ ላይ የሚገኙ ሰብሎች በእርጥበቱ እንዳይጎዱ በደረቅ ቀናቶች ውስጥ ሰብሉን መሰብሰብና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተጠቅሷል። በቀጣዮቹ 10 ቀናት በምዕራባዊና በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለዝናብ መኖር አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ ክስተቶች በይበልጥ እንደሚኖሩና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኤጀንሲው ትንበያውን አስቀምጧል። በተጨማሪም በነዚሁ ቀናት አልፎ አልፎ በጥቂት የደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያው መረጃ ያሳያል። በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአብዛኛው የላይኛውና አንዳንድ የታችኛው አዋሽና አንዳንድ የላይኛው የዋቢ ሸበሌና የኦጋዴን ተፋሶሶች ወቅቱን ያልጠበቅ ዝናብ ሊኖር እንደሚችልና የቀሩት የአገሪቷ ተፋሰሶች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩም ገልጿል። ይህ ሁኔታ ለበጋ ተጠቃሚ ተፋሰሶች የተሻለ የውሃ መጠን እንዲያገኙ የሚረዳ በመሆኑ የተፋሰሱ ተጠቃሚዎች የሚገኘውን ውሃ በተቻለ መጠን በመያዝ ለሚያስፈልገው አገልግሎት እንዲያውሉ ኤጀንሲው ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም