የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተጀመረ

72
ባህር ዳር ጥቅምት 13/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ  ስብሰባ በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀመረ። በስብሰባው የፓርቲው የ2011 የፖለቲካና የድርጅት ስራዎችን እቅድ በጥልቀት በመገምገም አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ አስታውቀዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ማዕከላዊ ኮሚቴው በ12ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ጉዳዮች የተቀመጡ አቅጣጫዎች ወደ ሕዝቡ በሚደርሱበት ጉዳይም በመምከር አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል። እንዲሁም ማዕከላዊ ኮሚቴውን የተቀላቀሉ አዲስና ነባር አባላት በአመራር ጥበብ ዙሪያ በሁለት ምሁራን በተዘጋጁ ጽሁፎች ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል ብለዋል። የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ አጃንዳዎችን በመለየትና ጥልቅ ግምገማ በማድረግ ቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥአቶ ምግባሩ አመልክተዋል። በስብሰባው የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ የመፍትሄ ሃሳቦች ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል። የፓርቲው ዝርዝር ተግባሮች በተዋረድ ለህዝብ በሚደርሱበት ሁኔታ ላይ የሚመክር የዞን አመራሮችን ያካተተ ግምገማ ጥቅምት 15ና 16/2011 እንደሚካሄድም ታውቋል። አዴፓ ባለፈው ወር ባካሄደው ጉባዔ 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና 13 የሥራ አስፈፃሚ አባላት መምረጡ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም